“276 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ግብር ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ሐምሌ እና ግብር” በሚል መሪ መልእክት የክረምት የግብር መሠብሠብ ሥራዎች የንቅናቄ መድረክን ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ምክትል ኀላፊ አበበ ደመላሽ የውይይት መነሻ ጹሑፍ አቅርበዋል።

በመነሻ ጹሑፋቸው በዘንድሮው የደረጃ ሐ እና የአከራይ ተከራይ ግብር 276 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለመሠብሠብ መታቀዱን ተናግረዋል። የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች እና የአከራይ ተከራይ ግብር የመክፈል መርሐ ግብር በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የግብር መክፈል ንቅናቄ በይፋ እየተጀመረ መኾኑን ተናግረዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጅዓለም ግብር መሠብሠብ እና የሰላም ሥራን አቀናጅቶ መሥራት ይገባል ብለዋል። የግብር መክፈል ሥራውን ለማቀላጠፍ ለግብር ማሠባሠብ የሚያግዙ ግብዓቶችን ማሟላት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኛው የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ግብር በተገቢው መልኩ ለመሠብሠብ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ግብርን በተገቢው ለመሠብሠብ መሪዎች እና ባለሙያዎች የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ቁርጠኛ ኾነው መሥራት እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።

ግብር የመሠብሠብ ሥራው ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲኾን ከተማ አሥተዳደሩ እስከ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር 23ሺህ 850 ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ከከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም የሁሉንም ጥረት ስለሚጠይቅ ተረባርቦ መስራት ይገባል” የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የኦዲት ግኝትን ዳር የሚያደርስ ቋሚ ኮሚቴ ሊያቋቋም ነው።