የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያዩ።

17

ባሕር ዳር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አኔት ቬበር (ዶ.ር) በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት ሁለቱ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሱዳን ሰላም ያደረጉትን ጥረት በበጎ ጎኑ አንስተዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሰላም ጥረት በመደገፍ እና በአፍሪካ ጥላ ማዕቀፍ ውስጥ የሱዳንን ሰላም ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው አመላክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ልዩ መልእክተኛዋ በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ጉዳዮች ዙሪያም ተወያይተዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረትን ስትራቴጂካዊ ትብብርን ለማሳደግ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ችግሮች በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ የመንግሥት ሠራተኛው ሀገራዊ ኀላፊነት አለበት” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር
Next article“ሰላም የሁሉንም ጥረት ስለሚጠይቅ ተረባርቦ መስራት ይገባል” የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች