
ጎንደር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የውይይቱን መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ካሳሁን ንጉሴ ውይይቱ በክልሉ ብሎም በዞኑ የገጠመውን የሰላም እጦት እና የፀጥታ ችግር በንግግር እና በውይይት ለመፍታት ያለመ ነው ብለዋል። የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ጥቅሞቻችን ላይ በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ደግሞ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው የሰላም እጦት የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም በበኩላቸው ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ተግባራትን የሚፈፅሙ መሪዎችን ለመፍጠር ኀላፊዎችን በሰለጠነ መንገድ መደገፍ እና መሞገት ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማፅናት ደግሞ ንግግር እና ድርድር እንደሚያስፈልግ ተናግረው አንድ ስንኾን እንጠነክራለን፤ እንከበራለን፤ ለዚህ ደግሞ የውስጥን ችግር በራስ የመፍታት ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ በትጋት ለመፈፀም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው ዘላቂ ሰላም የሚመጣው ሁሉም የበኩሉን ኀላፊነት መወጣት ሲችል ነው፣ ለዚህ ደግሞ አበክረን እንሠራለን ብለዋል።
የተጀመረው የሰላም እና የድርድር ሂደት ግቡን እንዲመታ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም በውይይቱ መልዕክት ተላልፏል።
ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!