
ባሕር ዳር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኩፍኝ በሽታ በሀገራችን ለህጻናት ሕመም፣ የአካል ጉዳት እና ሞት ምክንያት ከኾኑት በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በሽታው ኩፍኝ በሚባል ረቂቅ ተህዋሲያን በንክኪ እና በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፍ ነው።
በአማራ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ሲሰጥ የነበረው ክትባት በተገቢው መንገድ ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ በሽታው እየተስፋፋ መኾኑን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል። ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች ደግሞ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የአበርገሌ ወረዳ አንዱ ነው።
የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወንድሙ ደመቀ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት ለህጻናት ይሰጥ የነበረው ክትባት በመቋረጡ እና ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የኩፍኝ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል።
በ2016 ዓ.ም በወረዳው 525 ሰዎች መጠቃታቸውን እና የ16 ሰዎች ህይዎት ማለፉን በማሳያነት አንስተዋል። አሁን ላይ በመንግሥት የመከላከል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እናቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው እንዳሉት ደግሞ በአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም በ127 ወረዳዎች የኩፍኝ በሽታ ተከስቷል።
ከ6 ሺህ በላይ ህጻናት በበሽታው ተጠቅተዋል፤ 60 የሚኾኑት ደግሞ ህይዎታቸው አልፏል ብለዋል። የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል የህጻናትን የክትባት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ ማድረስ እንደሚገባ ያነሱት ዳይሬክተሩ ባለፉት 11 ወራት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ክትባት መስጠት የተቻለው 83 በመቶ ብቻ ነው።
በዚህ ወቅት ችግሩን ለመከላከል ክትባት ላልጀመሩ እና ጀምረው ላቋረጡ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት የቤት ለቤት ክትባት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ከሰኔ 27/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል። ከ740 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ህጻናት ኩፍኝን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች ክትባት እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!