
ባሕር ዳር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ እና ኢራን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረዚን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በውይይታቸው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ሁለተኛው የኢራን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል።
ኢትዮጵያ አዲስ ከተመረጡት ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኗንም ገልፀውላቸዋል።
በኢትዮጵያ እና በኢራን መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገውን ግንኙነት ለማሳደግ ብሪክስን ጨምሮ ሌሎች ግንኙነቶችን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የኢራኑ አምባሳደር አሊ አክባር ረዚን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በትምህርት፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ዝግጁ መዃኗን ገልፀዋል።
የኢትዮ ኢራን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ እና ቴክኒካል ትብብር ዙሪያ ለመወያየት ማቀዱንም አመላክተዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በኢትዮጵያ አዲስ ለተሾሙት አምበሳደር ቆይታቸው የተሳካ እንዲኾንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀውላቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!