
ባሕር ዳር: ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የዘርፉን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶች አበርክቷቸው ከፍ ያለ መኾኑ ተገልጿል፡፡
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሪዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ያላቸውን ሃብት ያለምንም ብክነት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዘርፉ ውስጥ የሚሠሩ ሁሉም ፕሮጀክቶች ዕቅዳቸውን ከግብርናው ዘርፍ የአምስት እና የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዶች ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ግልፀኝነት የተሞላበት ቅንጅታዊ አሠራር ሁሉም ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ በአግባቡ መሥራት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር ጽሕፍት ቤት ኀላፊ ግርማ በቀለ የውይይቱ ዋና ዓላማ የፕሮግራሙን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን የዘርፉ መሪዎች በተገኙበት መገምገም ነው ብለዋል፡፡ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ ከበሩ በላይነህ ፕሮግራሙ በ10 ክልሎች በ183 ወረዳዎች እና በ4 ሺህ 310 ቀበሌዎች ላይ እየሠራ የሚገኝ መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡
በመድረኩ ላይም የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲኾን በዕቅዱ ውስጥ ያልተካተቱ ሥራዎች እንዲካተቱ እና መሻሻል የሚጠበቅባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ ሃሳቦች መነሳታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!