
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተመረጡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን በማነጋገር 127 ሺህ 277 ቀበሌዎች ላይ የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎች ለአስፈጻሚ ተቋማት ለይተው አቅርበዋል፡፡
አስፈጻሚው አካል ለሕዝብ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳስቧል፡፡ ከህዝብ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማብራሪያ እየሰጡ ነው። የምክር ቤት አባላትም በተመረጡባቸው አካባቢዎች ወርደው ከ127 ሺህ 277 ቀበሌዎች የሰበሰቧቸው ጥያቄዎችም ለተቋማት ተለይተው ቀርበዋል።
የሰላም እጦት፣ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የመሰረተ ልማትና ፕሮጀክቶች መጓተት፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን አለማዳመጥ፣ የሚነገረውና መሬት ላይ ያለው መለያየት ዋና ዋና ጥያቄዎች መኾናቸውን በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴዔታ መሰረት ኃይሌ ተናግረዋል።
በተቋማቱ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ.ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
በዚሁ ወቅት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ.ር)÷ ለሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ መንግስት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በበኩላቸው÷ የኅብረተሰቡ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው የፀጥታ ችግር በተፈለገው ያህል የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን ተጠቅሞ የተገዛውን ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ እየተሠራ መኾኑንና የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በእጀባ እየተሰራጨ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ኤፍቢሲ እንደዘገበው ማዳበሪያ እጥረት ችግር የማይኾንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ አዳዲስ የግዥና የማጓጓዝ ሥርዓቶች እየተዘረጉ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ.ር)፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየውን የሀብት ብክነትና ሙስና ለማስቆም እስካሁን የ6 ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች መነሳታቸውን ጠቅሰው፤ በመጪ ሳምንታትም የ4 ተቋማት መሪዎች እንደሚነሱ ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!