ታራሚዎች ራሳቸውን ከኮረና ቫይረስ ስርጭት እንዲከላከሉ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች መምሪያ አስታወቀ፡፡

162

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ናኪ ሆቴልና ስፓ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ለሚገኙ ታራሚዎች አንድ ሺህ ሊትር ፈሻሽ ሳሙና አበርክቷል፡፡ ፈሳሽ ሳሙናው ታራሚዎች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ያለመ ነው፡፡ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ሽፈራው ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የመኖር ሥጋት እየሆነ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ ድርጅታቸው ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ቫይረሱ የሚያደርሰውን ጉዳት ከወዲሁ ለመከላከል ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ታራሚዎች የንጽሕና መጠበቂያ ማቅረቡ የድርጅቱ ግዴታ እንጅ ዕርዳታ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አስታውቀዋል፡፡ በሽታው ተከስቶ በሰዎች ሕይወትና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ እንቅፋት ከመፍጠሩ በፊትም ተመሳሳይ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ሆቴሎ እንደሚያቀርብም ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም ሲቋቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በገቡት ቃል መሠረት በዚህ ፈታኝ ወቅት ወገናዊ አለኝታነቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች መምሪያ መሠረታዊ ፍላጎትና ጤና አገልግሎት ቡድን መሪ ኮማንደር አስራት ዓድማሱ ታራሚዎች ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ከውጭ ከሚመጡ ማንኛውም ግለሰብ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡና አዲስ ታራሚ መቀበል እንዳቆሙም ተናግረዋል፡፡ የታራሚዎች ሰብሳቢ ወጣት ታየ ልይህ የተደረገላቸው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፤ ስለተደረገላቸው ሁሉም ምሥጋና አቅርቧል፡፡

በመምሪያው የሚኒ ሚድያ ማዕከል ተጠቅመው ስለበሽታው መተላለፊያና መከላከያ ዘዴዎች እርስ በርስ እየተማማሩ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleበአሁኑ ጊዜ ዘጠኝ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
Next articleበኩር መጋቢት 21-2012 ዓ/ም