“ወጣቶች በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን መልካም እድል ለመጠቀም ከማንም በላይ በሀገራዊ ምክክሩ ባለድርሻ ሊኾኑ ይገባል” ኮሚሽነር አምባየ ኦጋቶ (ዶ.ር)

10

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዘመናት መካከል የዘለቀ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ቁርቁስ ለአሁናዊው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ፈተና የኾነባት ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሁነኛ ፈውሷ ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡ ለዘመናት በነፍጥ እና በነውጥ የዘለቀችው ኢትዮጵያ በግጭት እና ጦርነት የመጣችባቸው እልህ አስጨራሽ መንገዶች ከወጪ ቀሪያቸው ቢሰላ ትርፉ ጉስቁልና ብቻ ነበር፡፡

አሮጌውን እና ቀላሉን የግጭት መንገድ ለመጨረሻ ጊዜ ቋጭቶ አዲሱን እና ፈታኙን የንግግር እና ምክክር ሂደት ለመጀመር አሁናዊቷ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው፡፡ ምክክሩ የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና የፖለቲካ ልሂቃንን ተሳትፎ ብቻ የሚጠይቅ እንዳልኾነ ይታመናል፡፡ ምክክሩ የኢትዮጵያ በመኾኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑም ይጠበቃል፡፡

በሀገሪቱ 70 በመቶ የሚኾነውን የሕዝብ ቁጥር የሚሸፍነው ወጣቱ ትውልድ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የላቀ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባየ ኦጋቶ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ ወጣቶች በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን መልካም እድል ለመጠቀም ከማንም በላይ ባለድርሻ ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሀገሪቱ የዘመናት ሀገረ መንግሥት ምስረታ ሂደት ውስጥ ግጭት ግጭትን እየወለደ ሞት እና መገዳደል ለውጥ እንዳላመጣ አይተናል ያሉት ኮሚሽነር አምባየ አዲሱን የንግግር እና የምክክር መንገድ መሞከር ይኖርብናል፤ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ድርሻቸው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ በላይ ግጭቶች ተፈጥረው አይተናል ያሉት ኮሚሽነሩ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በምን አይነት የግጭት አዙሪት ውስጥ እንዳለች ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ወጣቶች ከየትኛውም ተፅዕኖ ነጻ ኾነው ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን የደርሻቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ነባሩ የፖለቲካ ምህዳር መደማመጥ የራቀው እና ተናጋሪው የበዛበት መኾኑን ያወሱት ኮሚሽነሩ የሰከነ እና የሰለጠነ ምክክር ማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀው መንገድ ነው ብለዋል፡፡ በስክነት ስንነጋገር ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ዐይን የምትመለከት ኢትዮጵያም እውን ትኾናለች ነው ያሉት፡፡

እንደ ኮሚሽነር አምባየ ገለጻ የበርካታ ሀገራት ተሞክሮ የሚያመላክተው ከገጠማቸው ችግር እና ካለባቸው ጥቁር ጠባሳ እንዲሽሩ ወጣቱ ትውልድ አይተኬ ሚና ተጫውቷል፡፡ “እኛ ግን የቀደመ ታሪካችንን መጋፈጥ ፈርተናል” ያሉት ኮሚሽነሩ ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ ዳር ቆመው ተመልካች ሳይኾኑ ባለቤት እንዲኾኑ ጠይቀዋል፡፡

ወጣቶች በሀገራዊ የምክክር ሂደት ድርሻቸው እና ተሳትፏቸው ምን መኾን እንዳለበት ራሳቸውን በመጠየቅ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልቃይት ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ56 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እየሠራ መኾኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ዙር የ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ የ12ኛ ክፍል የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ዛሬ መፈተን ጀምረዋል።