96 በመቶ የ12ኛ ክፍል የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተና ወልድያ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

34

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ እና አላማጣ ከተማ እንዲሁም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኦፍላ እና ኮረም አካባቢዎች የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ዝግጁነት ድጋፍ እና የማካካሻ ትምህርት ሲሰጣቸው መቆየቱን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዛሬ ይጀመራል፡፡ ለወራት ግጭት ውስጥ የቆየው የአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በችግር ውስጥም ኾነው የመማር ማስተማሩን ሥራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይም በበርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን ለመውሰድ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ከሚገኙ 15 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የመጡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፡፡ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰጠ ታደሰ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ 96 በመቶ የ12ኛ ክፍል የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተና ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል ብለዋል፡፡

በዞኑ ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ እና አላማጣ ከተማ እንዲሁም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኦፍላ እና ኮረም አካባቢ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ሲዘጋጁ መቆየታቸውን መምሪያ ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡ ከ800 በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው መምህራን መድቦ የማካካሻ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሰጠ በአካባቢው በነበረው ግጭት ምክንያት እንዳይረበሹ ተማሪዎችን በሥነ ልቦና የማዘጋጀት ሥራዎችም ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ ከተፈታኝ ተማሪዎች እና ከፈታኝ መምህራን ውጭ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባት እና መውጣት ስለማይቻልም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ቦታ ተመቻችቶላቸው ከግቢ እንዲወጡ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና ሲጠናቀቅም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ወደ ግቢ ይመለሳሉ ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ ፈተናቸውን በተረጋጋ ኹኔታ እንዲፈተኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለሠሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምሥጋና ያቀረቡት መምሪያ ኀላፊው በተለይም ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ኀላፊነቱን ወስዶ ለሠራቸው ሥራዎች ላቅ ያላ ክብር አለን ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጊዜውን የዋጀ ተቋማዊ አሠራርን በመዘርጋት የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።
Next articleየ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀምሯል።