
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና የገጠር መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶችን መልሶ ለማደራጀት ተሻሽሎ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በክልሉ የውኃ እና ፍሳሽ ተቋማት አደረጃጀቶችን ለማጠናከር እና የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ተሳትፎ ለማሳደግ የኢትዮጵያ የውኃ ሃብት አሥተዳደር ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ በአማራ ክልል በገጠር አካባቢዎች በሚገኙ የውኃ ተቋማት ራሳቸውን የቻሉ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር፣ ከወቅቱ ጋር የተናበቡ ዘመናዊ አሠራሮችን ለመዘርጋት ብሎም የፍሳሽ አወጋገድ፣ አሥተዳደር እና አጠቃቀምን ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል አዋጁን ለማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።
በአማራ ክልል አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ እጅግ ወሳኝ ነውም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ዘርፉን ለማዘመን፣ የውኃ እና ፍሳሽ አግልግሎትን እና አሥተዳደርን ለማሳለጥ፣ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ተቋማትን ለመገንባት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ጊዜውን የዋጀ ተቋማዊ አሠራርን በአዋጅ ታግዞ በመዘርጋት ከመጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የከተማ እና የገጠር መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶችን መልሶ ለማደራጀት ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በርካታ ባለሙያዎች እና መሪዎች የተሳተፉበት ነው። ረጅም ጊዜ የወሰደ እና ወቅቱን የዋጀ በመኾኑ በቀጣይ የተሰጡ አስተያየቶች ታክለው እንደሚጸድቅ ዋና አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!