
ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ሀገራዊ ምክክሩ በውይይት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ኢትዮጵያ በምክክር ችግሮቿን ለመፍታት የነበሯት በርካታ ዕድሎች እና አጋጣሚዎች አምልጠዋት እስካሁን መዝለቋን አስታውሰዋል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ በምክክር ችግሮቿን እንደምትፈታ እና በዋና ዋና ጉዳዮችም ሀገራዊ መግባባት መፍጠር እንደምትችል ጽኑ እምነት ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አምባሳደር መሐሙድ ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሚመራው መንግሥት ለምክክሩ ጉልህ ስፍራ በመስጠት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጉ የዘመናትን የሕዝብ ጥያቄ የመለሰ መኾኑን ገልፀዋል። ለምክክሩ ሂደት መሳካት መንግሥት በቁርጠኝነት ድጋፍ እና እገዛ በማድረጉ ጭምር ምክክሩ እስካሁን በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የምክክሩ ሂደት የቅድመ-ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የምክክር እና የክትትል ምዕራፎች ያሉት መኾኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ የኾነ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ኾኖ በ2014 ዓ.ም በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!