
ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ውይይት እያደረጉ ነው። የእድሜ ባለጸጋ የኾኑት ታፈረ ዳኛው የሰው ሕይዎት እንዳይጠፋ፣ የሀገር ሃብት እንዳይወድም፣ የሴራ ፖለቲካው ምዕራፍ እንዲዘጋ እና ሰላም እንዲሰፍን ውይይት ኹነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል።
አቶ ታፈረ ዳኘው መንግሥት እና ጫካ የገቡ ወገኖች በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ተረድተው ወደ ውይይት በመምጣት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ዜጎቿንም ከዕልቂት የመታደግ የዜግነት ግዴታ አለባቸው ነው ያሉት። ይህ ጦርነት ከቀጠለ ሀገር ከአሁኑ የባሰ እንደምትወድም ተናግረው ሁሉም ወገኖች ሕዝባቸውን ከዘርፈ ብዙ ስቃይ እንዲታደጉት ጠይቀዋል።
መሪጌታ ኪነ ጥበብ ሰላም መቼ ነው የሚመጣው እያሉ ሲጨነቁ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን የሰላም ጥሪ በመቅረቡ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ሁሉም ወገኖች ለኢትዮጵያ ያስፈልጓታል ያሉት መሪጌታ ኪነ ጥበብ መንግሥትም ኾነ በጫካ ያሉ ወንድሞች ስለሕዝብ ብለው ልዩነትን በውይይት በመፍታት ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊ ሸህ ጡሃ “ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው። ሁሉም ሰው ለሰላም በመጨነቅ እና በመጠበብ ሀገራዊውን ችግር በውይይት መፍታት ተገቢ ነው ብለዋል። ግጭት ውስጥ የገቡት ሁሉ ልጆቻችን ናቸውና ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር የእነርሱን መስማማት ያስፈልገናል ብለዋል። እኛም በየቤተ እምነታችን ስለሰላም እናስተምራለን እንጸልያለንም” ነው ያሉት።
የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ተዋበ አንለይ እንዳሉት የውይይቱ ዓላማ ኀብረተሰቡ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ በሰላሙ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በሁሉም ዘንድ አጀንዳ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት። ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አክለውም እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ገጭቶችን እና ጦርነቶችን ማስቀረት የሚችለው ኀብረተሰቡ በችግሩ ዙሪያ በንቃት ሲወያይ ነው ብለዋል።
አቶ ተዋበ ኀብረተሰቡ አሉ የሚላቸውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በሕግ እና በሥርዓት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማቅረብ ለቁርሾ የሚዳርጉ ጉዳዮችን መልስ በማሰጠት ደም መፋሰስን ማስቀረት ይቻላል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!