ከ873 ሺህ በላይ ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ።

292

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር አዘዞ ክፍለ ከተማ 873 ሺህ 900 ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር 5ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቻላቸው የኔነህ ጥቆማው ከማኅበረሰቡ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ከኢፌዴሪ ጉምሩክ ባለስልጣን የጎንደር ከተማ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ እና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ መረጃ ክፍል ጋር በተሠራ ኦፕሬሽን ሐሰተኛ ገንዘቡ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተናግረዋል።

አንድ ግለሰብ ከነግብረ አበሮቹ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዋና ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል፡፡ ዋና ተጠርጣሪው በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ስሞች የሚጠራ እና በሐሰተኛ መታወቂያዎች የሚንቀሳቀስ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።

ፖሊስ እንዳለው 873 ሺህ 900 ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ጨምሮ ዘጠኝ ኪሎ ግራም የሚመዝን ነሐስ፣ ጌጣጌጦች፣ ማዕድናት፣ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች የሚመስሉ ሐሰተኛ ቁሶች፣ የሐሰተኛ ዶላር ኖቶች ማባዣ ማሽን እና ሌሎች ዕቃዎች ጋር ነው ተርጣሪዎቹ የተያዙት።

በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር የገባ መኪናም (ላንድ ክሩዘር) በኢግዚቢትነት መያዙን ዋና ኢንስፔክተር ቻላቸው ገልፀዋል። ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ትናንት መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም በአዘዞ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20 አባ ሳሙኤል በሚባል አካባቢ ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ነው።

ዋና ተርጣሪው “የማዕድን ማውጫ ፈቃድ አለኝ፤ ወርቅ አወርዳለሁ፤ እና የሰውን ልብ አውቃለሁ” በማለት ሲያጭበረብር እንደነበርም ነው ፖሊስ የገለፀው።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም በጥቅሉ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ማጭበርበር የተፈፀመባቸው ግለሰቦች እያመለከቱ እንዳሉ ፖሊስ አስታውቋል። ማኅበረሰቡ ብር በግለሰብ ደረጃ የሚታተም አለመሆኑን በመገንዘብ በአጭበርባሪዎች እንዳይታለልም ዋና ኢንስፔክተር ቻላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ

Previous articleየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡
Next articleበአሁኑ ጊዜ ዘጠኝ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡