“የታሪክም የትውልድም ተወቃሽ ላለመኾን ጦርነት ይብቃን” በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች።

13

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል። በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ማኅበረሰቡ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረገ መኾኑን የኮንፈረሱ ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች አንስተዋል።

አሁን ላይ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር የመንግሥት ሠራተኛው በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዳይገባና ለኅብረተሰቡ ተገቢውን ማኅበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ ስጋት ማሳደሩንም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። የግል ጥቅመኞች አሁን ያለውን የጸጥታ መደፍረስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በእገታ እና በግድያ ወንጀል ተሰማርተው የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገደብ ማድረጋቸውንም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን በማባባስ የመንግሥት ሠራተኛውን ጨምሮ በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ህይወቱ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲኾን አድርጓል ብለዋል ተሳታፊዎቹ። በመኾኑም ትጥቅ አንግበው ጫካ የገቡ ኀይሎች በሰላም ካውንስሉ የቀረበውን የመፍትሔ አማራጭ ተቀብለው ወደ ሠላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ የጋራ ርብርብ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

ጦርነት አውዳሚ እና አክሳሪ መኾኑን ከሰሜኑ ጦርነት ልንማር ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ “የታሪክም የትውልድም ተወቃሽ ላለመኾን ጦርነት ይብቃን” ብለን በጦርነት የተጎዳውን ሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ሠላምን በማስፈን ልንክሰው ይገባል ብለዋል። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጸጥታ መዋቅሩ ተግባር እና ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የመንግሥት ሠራተኛው ኀላፊነት ጭምር ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ሰላምን ለማምጣት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ በጫካ ያሉ ኃይሎች ለውይይት እና ለድርድር እንዲቀርቡ እንዲሁም የሕዝብን ሰላም እና ደሕንነት ለማረጋገጥ እንዲሠሩ የመንግሥት ሠራተኛው የሚጠበቅበትን ማድረግ አለበት ብለዋል። በክልሉ የሰላም ካውንስል የቀረበው የሰላም አማራጭ እና የድርድር ሃሳብ ውጤት እንዲያመጣ ለተግባራዊ ተፈጻሚነቱ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ከንቲባው አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእንሳሮ ወረዳ አርሶ አደሮች በአካባያቸው ሰላም ዙሪያ መከሩ፡፡
Next articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይዎታቸው እንደሚመለሱ ተናገሩ።