
ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ከይድኖ እና በሬሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች አካባቢያቸውን ሰላም ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ የአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ወጥቶ ለመግባትም ኾነ የግብርና ሥራቸውን ለማካሄድ አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ አርሶ አደሮቹ ባለፉት ጊዜያት በቀያቸው የነበረው የሰላም እጦት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዳርጓቸው ስለመቆየቱ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ግብዓት እና ምርጥ ዘር ለማግኘት የሰላም እጦት አስቸጋሪ አድርጎባቸው እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሮቹ አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማዝለቅ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ የሰላም ጉባኤ የቀረበውን የሰላም ጥሪ በደስታ እንደሚቀበሉት የተናገሩት አርሶ አደሮቹ ሁሉም ከሰላም ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ የእንሳሮ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ እንደሚያመላክተው ታጥቀው በጫካ የሚገኙ ወገኖችም ለሕዝባቸው ሰላም መኾን የበኩላቸውን እንዲወጡ እና ለውይይት በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!