
ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እናቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው እንዳሉት እናቶች በእርግዝና፣ በምጥ እና በወሊድ ጊዜ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር ለመከላከል በጤና ተቋማት ተገኝተው ክትትል እንዲያደርጉ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
እናቶች በጤና ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉ በተሠራው ተከታተይ ሥራ እስከ አራት ጊዜ በጤና ተቋማት ያደርጉ የነበረውን ክትትል እስከ ስምንት ጊዜ ማድረግ እንዲችሉ ተደርጓል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት 11 ወራትም 65 በመቶ ነፍሰ ጡር እናቶች አራት ጊዜ እና 20 በመቶ ስምንት ጊዜ በጤና ተቋማት ክትትል አድርገዋል። 58 በመቶ እናቶች ደግሞ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ተሠርቷል። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት ከነበረው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ነፍሰ ጡር እናቶች ቢያንስ አንድ ጊዜ በጤና ተቋማት ክትትል ያደርጉ እንደነበር ዳይሬክተሩ አንስተዋል። በዚህ ዓመት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ክትትል ያደረጉት ግን 83 በመቶ ብቻ ናቸው። በክልሉ ካሉት 613 የእናቶች ማቆያ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ከግማሽ በታች ናቸው። በክልሉ ካሉት አንቡላንሶች ውስጥ አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙት ውስን መኾናቸውን አንስተዋል።
በግጭቱ ምክንያት ነፍሰ ጡር እናቶች በየአካባቢያቸው ተሰባስበው እንዲመካከሩ ማድረግ አልተቻለም። ግብዓትን በተፈለገው መንገድ ያለማቅረብ ችግሮች ማጋጠሙንም አንስተዋል። ጤና ተቋማት ለማኅበረሰቡ በተሟላ መንገድ አገለግሎት እንዲሰጡ ሀሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!