የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሰላም አማራጭን መከተል እንደሚገባ የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

10

እንጅባራ: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር “ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም በክልሉ የተፈጠረው ግጭት የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ በርካታ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን መፍጠሩን ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የጋራ ጥያቄዎቻችን ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሰላም አማራጭን መከተል እንደሚገባም አንስተዋል።

በክልሉ የቀጠለው ቀውስ መቋጫውን እንዲያገኝ ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ መኾን እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ በውቀት ቢተው በከተማ አሥተዳደሩ ከ4 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው የተለያዩ የሰላም መድረኮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

በተካሄዱ መድረኮችም ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት አሳይቷል ነው ያሉት። በከተማ አሥተዳደሩ ወጣቶችን ወደ አልተፈለገ ተግባር የሚገፉ የሥራ እድል ፈጠራ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ኀላፊው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ ሳይወስን እና ሳያምንበት የትምህርት ቤት ክፍያ መጨመር እንደማይቻል የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ፡፡
Next articleወጣቶች በሀገራዊ ምክክሩ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።