
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ የ2016 የትምህርት ዘመን አፈጻጸም እና የ2017 የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በ2016 የትምህርት ዘመን በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት 56 ትምህርት ቤቶች የስድስተኛ ክፍል፣ 47 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የስምንተኛ ከፍል ተማሪዎችን ማስፈተናቸውን ተናግረዋል። ፈተናዎቹ ሰላማዊ በኾነ መንገድ መጠናቀቃቸውንም አስታውሰዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን የጸጥታ ችግሩ ፈተና እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው ጭስ ዓባይ፣ መሸንቲ እና ዘጌ ትምህርት ቤቶች ማስፈተን አለመቻላቸውንም ገልጸዋል። በትምህርት ዘመኑ ከ128 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የመንግሥት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር መሠራቱን ነው የተናገሩት።
የመማር ማስተማር ሥራውን ለማጠናከር ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። ትምህርቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ መምህራን፣ ተማሪዎች ወላጆች እና ሌሎች የትምህርት መሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የ2017 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅ ሥራ ከአሁኑ መጀመሩንም አስታውቀዋል። የ12ኛ ክፍል ፈተና እንደተጠናቀቀ ወደ ክረምት ሥራዎች እንደሚገቡም ገልጸዋል። የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በከተማዋ 46 የአንደኛ ደረጃ እና 10 የሁለተኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ያነሱት ኀላፊው ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪ ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ነገር ግን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።የግብዓት እና የትምህርት ሂደት ችግር ያለባቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ነው ያስረዱት።
በተደረገው ክትትል ስምንት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ኾነው በመገኘታቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጡ ነው የተናገሩት። በክረምቱ ወቅት አስተካክለው ሥራቸውን የሚቀጥሉበት ዕድል አለ፣ ማስተካከል ካልቻሉ ግን በ2017 የትምህርት ዘመን መቀጠል አይችሉም ነው ያሉት። ትምህርት ቤቶች የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የተሟላ ቢሮ እና መጸዳጃ ቤቶች የሌሏቸው፣ የሰው ኀይል ያላሟሉ እና ሌሎች ማሟላት የሚገባቸውን ግብዓቶች ሳያሟሉ የተገኙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ፈቃድ ሳይኖራቸው ሢሠሩ የተገኙ ትምህርት ቤቶች መገኘታቸውንም ገልጸዋል። ደረጃዎችን ማሟላት የማይችሉት በ2017 የትምህርት ዘመን እንደማይቀጥሉም ተናግረዋል። የቅድመ መደበኛ ትምህርት ፈቃድ ወስደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምረው የተገኙ መኖራቸውንም ገልጸዋል። ዕውቅና ያልተሠጣቸው ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሂደት አይቀጥሉም ነው የተባለው።
አምስት ትምህርት ቤቶች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ከመስጠታቸው ታግደው ቅድመ መደበኛ ብቻ እንዲያስተምሩ ተወስኗል ነው ያሉት። ሁለት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ መታገዳቸውን ነው የተናገሩት። ፈቃድ ባልተሰጠው ትምህርት ቤት የተማሩ ተማሪዎች እንዳልተማሩ እንደሚቆጠር እና በዚያ ያገኙትን ውጤት ይዘው በየትኛውም ትምህርት ቤት ገብተው መማር እንደማይችሉ ነው የገለጹት።
ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስመዝገባቸው በፊት ስለ ትምህርት ቤቶች ማወቅ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት። በመመሪያው መሠረት የትምህርት ምዝገባ የሚጀምረው ከሐምሌ 15 ጀምሮ ነው ያሉት ኀላፊው ከመመሪያ ቀድመው ተማሪ መሻማት በሚመስል መልኩ ቀድመው እየመዘገቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። መዝገባ ያለ ወቅቱ የጀመሩ ትምህርት ቤቶች ላይ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ነው የገለጹት።
ከመመሪያ ውጭ ጭማሪ መጨመር በማኅበረሰቡ ላይ ጫና እየፈጠረ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ከግንቦት 30 በፊት ማኅበረሰቡ ተሠብሥቦ በጭማሪው ዙሪያ ተወያይቶ በመግባባት ውሳኔ ካልሰጠ በስተቀር የክፍያ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ነው ያሉት። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በደብዳቤ ብቻ ጭማሪ እየጨመሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ከሕግ እና ከመመሪያ የወጣ ጭማሪ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።
ማኅበረሰቡ ሲፈቅድ ጭማሪ ለማድረግ ትምህርት መምሪያው ፈቃድ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ሳይስማማ በደብዳቤ ብቻ ጨምረናል የሚሉ ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጥሪ አቅርበዋል። ተቋማቱ አካሄዳቸውን ማስተካከል እንደሚገባቸው እና ማኅበረሰቡም መብቱን ማስከበር አለበት ነው ያሉት። መሪዎችም ከሕግ እና መመሪያ ውጭ የሚሠሩ ትምህርት ቤቶችን መቆጣጠር እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት። የጸጥታ አካላትም ሕግ እንዲያስከብሩ ጠይቀዋል። ትምህርት መምሪያው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕግ እንደሚያስከብርም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ በግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ የሚደርስበትን ጫና ለመቀነስ መፍትሔው የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ጥራት ማዘመን እንደኾነም ተናግረዋል። የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመቀበል አቅማቸው እንዲጨምር፣ ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ማድረግ ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል። ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ተወዳዳሪ ከኾኑ ማኅበረሰቡ ክፍያውን ትቶ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን እንደሚመርጥ ነው የተናገሩት።
በከተማዋ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን የትምህርት ጥራት የማሳደግ እና ለሌሎች አርዓያ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ተወዳዳሪ የኾኑ ትምህርት ቤቶችን የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!