
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጥናት የተለዩ ማዕድናትን ጥቅም ላይ ለማዋል ባለሀብቶችን የማሣተፍ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
የዞኑ ማዕድን መምሪያ ኅላፊ የሽሀረግ መለሰ እንደገለጹት በአካባቢው እንደ ብረት፣ ሊትየም እና ሌሎች ለግንባታ የሚውሉ ማዕድናት በጥናት ተለይተው ወደ ምርት እንዲገቡ ለባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። ነገር ግን በክልሉ ያጋጠመው ቀውስ የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ ለማልማት እንዳላስቻለ ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ በግንባታ ቁሳቁስ ምርት ከ21 በላይ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ የገቡ ሲኾን አራት ኢንዱስትሪዎች ምርት ማምረት ጀምረዋል፡፡ በተገኘው አንጻራዊ ሰላም የማዕድን ዘርፉን ለማልማት ባለሀብቶችን የመደግፍ ሥራም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር መኾኑን ኅላፊዋ ተናግረዋል፡፡ የዞኑን የተፈጥሮ ጸጋ ለማልማት ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ ባለሀብቶች ለሰላም መረጋገጥ ኅለፊነታቸውን እንዲወጡ እና የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች እንዲያስቀጥሉ ኅላፊዋ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በግንባታው ዘርፍ ከውጭ ሊገባ የነበረን ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀረት መቻሉም ተነግሯል።
ዘጋቢ፡ የኔነህ አለሙ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!