የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡

690

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና
ለመቆጣጠር የኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል እና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ይርሳው ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
-በርእሰ መስተዳድሩ የሚመራ፤ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሮች፣ ሠላምና ደኅንነት፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ፣ ጤና ቢሮ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ያለበት የኮሮና ቫይረስ መከላከል እና መቆጣጠር ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡

– የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር የሚመራ ሆኖ 20 የቢሮ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያለበት 5 የቴክኒክ ኮሚቴዎችን አዋቅሯል፤ ኮሚቴውም የሕክምናና የብክለት መከላከል፣ የወረርሽኝ አሰሳና ቅኝት፣ የግብዓትና የፋይናንስ፣ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን እና የሀብትና ድጋፍ ማፈላለግ ሥራ የሚሠራ እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በክልሉ እስካሁን 11 ተጠርጣሪዎች እንደነበሩ እና ሁሉም ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡ ዛሬ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር የክልሉ መንግሥት ካለፈው የቀጠሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

በዚህም መሠረት ከዛሬ መጋቢት 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ በአንድ ቦታ ላይ መቆየት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ተጋላጭነት ለመቀነስ በየተቋማቱ ኃላፊዎች የሚተገበሩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ እነርሱም ነብሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው የደረሱ ሠራተኞች፣ አንገብጋቢና አስቸኳይ ሥራ የሌለባቸው የሥራ ክፍል ሠራተኞች፣ የቆየ እና በሐኪም ማስረጃ የተደገፈ የጤና እክል ያለባቸው ሠራተኞች፤ የተለየ ተለዋጭ ማብራሪያ እስኪሰጥ ድረስ በቤታቸው ሁነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተወስኗል፡፡

ይህ ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የፀጥታ አካላት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከምንጊዜውም በላይ አሁን ካጋጠመው ችግር እስኪወጣ ድረስ ሥራቸውን በከፍተኛ ሕዝባዊ ኃላፊነት እና ተቆርቋሪነት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም ጊዜ የማይሠጡ እና አንገብጋቢ የሆነ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንደ የመብራት፣ የውሀ እና የትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማትም በሙሉ አቅማቸው ሕዝባቸውን እንዲያግዙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የክልሉ መንግስት ከምንግዜውም በላይ ያለውን አቅምና ትኩረት በሙሉ እዚሁ ተግባር ላይ በማድረግ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በሕዝቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ መላው የክልሉ ሕዝቦችም ያላቸው አቅም አስቀድሞ መከላከል መሆኑን በማወቅ የሚሠጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የክልሉ መንግስት በጥብቅ አሳስቧል፡፡ አላስፈላጊ ስጋት፣ አላስፈላጊ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ተብሏል፡፡

በየደረጃው ማለትም ከክልል እስከ ታችኛው እርከን ያሉ የተቋማት አማራሮች የክልሉን መንግሥት ውሳኔ ባፋጣኝ ተግባራዊ በማድረግ ለክልሉ ግብረ ኃይል ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባቸው ያመላከተው መግለጫው ለተግባሩ የተለየ ትኩረት በመስጠት የየዕለቱን እንቅስቃሴዎች ለግብረ ኃይሉ እንዲያሳውቁም ነው መግለጫው የጠቆመው፡፡

የግብረ ኃይሉ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮሚቴም በየዕለቱ የሚደርሱትን መረጃዎች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

Previous articleስለ ኮሮና ቫይረስ ዕለታዊ መረጃዎች
Next articleከ873 ሺህ በላይ ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ።