ካሜላ ሀሪስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ተክተው ለምርጫ ይወዳደሩ ይኾን?

20

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወቅቱ የአሜሪካ ፕረዚዳንት ጆ ባይደን ምክትል የኾኑት ካሜላ ሀሪስ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደንን ተክተው እንዲወዳደሩ የሚመጡ ግፊቶችን የተቀበሏቸው አይመስልም።

ይልቁንም እሳቸው ለአለቃቸው ሲሞግቱ ነው የሚደመጡት። የ59 ዓመቷ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሜላ ሀሪስ የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን የዲሞክራቶች እጩ ኾነው ምርጫውን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያምናሉ። “ጆ ባይደን በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ያመጧቸው ውጤቶች በ90 ደቂቃ ክርክር ዋጋ ሊያጡ አይገባም” ሲሉም ካሜላ ሀሪስ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ጆ ባይደን ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ በ ሲ ኤን ኤን ክርክር ላይ በጣም ደካማ አቋም ካሳዩ በኃላ ዲሞክራቶች እና የፓርቲው ደጋፊዎች ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ምርጫውን ለማሸነፍም ከ ጆ ባይደን የተሻለ እጩ ማቅረብ እንደሚገባም እየተናገሩ ነው። የባይደን ምክትላቸው ካሜላ ሀሪስ ደግሞ ትክክለኛዋ እጩ እንደኾኑ እየተነገረ ነው።

ካሜላ ሀሪስ የሪፐብሊካኑን እጩ ዶናልድ ትራምፕን በጥሩ ሁኔታ ማሸነፍ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በበርካቶች ዘንድ የባይደን ትክክለኛ ተተኪ ተደርገው የሚወሰዱት ካሜላ ሀሪስ እስከ ዛሬ ድረስ አለቃቸውን የሚያሳጣ አይነት ተግባር እና ንግግር ውስጥ አልገቡም ይላል ቢቢሲ።

ባለፈው ቅዳሜ በኒው ኦርሊንስ የጥቁሮች የባሕል ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ፕሬዚዳንት ካሜላ ሀሪስ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ስለ ግል ሕይወታቸው እና በነጩ ቤተ መንግሥት ስላከናወኗቸው ተግባራት ገለጻ አድርገዋል። የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር እና የደቡብ እስያ ዝርያ ያላቸው አሜሪካዊት ምክትል ፕሬዚዳንት ካሜላ ሀሪስ በዚህ መድረክ ያደረጉት ንግግር በአይነቱ ልዩ የሚባል ነበር።

በአብዛኛው ባይደንን እየተከተሉ ንግግር ሲያደርጉ ለቆዩት እና ሀሳባቸውም በተሟላ መንገድ ሲተላለፍ ላልነበረው ካሜላ ሀሪስ ይህ መልካም አጋጣሚ ነበር። በ ጆ ባይደን አቋም ደስተኛ ያልኾኑት ዲሞክራቶች ፕሬዚዳንቱን ተክተው በቀጣዩ ምርጫ እንዲወዳደሩ ግፊት የጠነከረባቸው ካሜላ ሀሪስ ስለ ባየደን አቅም ሲጠየቁ ምንም አይነት መጥፎ ነገር አልተናገሩም።

በቅዳሜው መድረክ የተናገሩት ንግግር ግን ስለ ወደፊት የፖለቲካ ሕይወታቸው ፍንጭ የሰጠ ነበር። በኒው ኦርሊንስ መድረክ ላይ ንግግራቸውን ሲከታተል ለነበረው ሕዝብ አትችሉም የሚለውን ትችት እንዳይቀበሉ መክረዋል። ካሜላ ሀሪስ “በሕይወታችሁ ውስጥ ሰዎች ጊዜው የእናንተ አይደለም፣ የእናንተ ተራ አይደለም፣ ማንም እንደዚህ ሠርቶ አያውቅም የሚሉ ነቀፌታዎች ሊሰነዘሩባችሁ ይችላሉ ይህን ስምታችሁ ግን ከአላማችሁ አትመለሱ” ሲሉ በራስ መተማመን ስሜታቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከየቦታው ጫናዎች ቢበረቱባቸውም እስካሁን የዲሞክራቶች እጩ ኾነው እንደቀጠሉ ናቸው። ምናልባት እጬነታቸውን ለምክትላቸው አሳልፎ ይሰጡ ይኾን የሚለውም በቀጣይ መልስ የሚያገኝ ይኾናል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገሪቱ የወደፊት ተረካቢ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ በሀገራቸው ቀጣይ እጣ ፋንታ በጋራ የመወሰን መብት አላቸው” ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ
Next articleከአዲስ አበባ ተሞክሮ በመውሰድ የልማት ሥራዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት ያለመ ጉብኝት እየተካሄደ ነው፡፡