
አዲስ አበባ: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የወጣቶች ሚና እና ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር” በሚል የፓናል ውይይት መድረክ እያካሄደ ነው። በመድረኩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ የሀገሪቱ የወደፊት ተረካቢ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ እና በሀገራቸው ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ በጋራ የመምከር እና በጋራ የመወሰን መብት አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ አካታች እና አሳታፊ በኾነ መንገድ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ መምከር እና በጋራ መወያየት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ መድረኩ የወጣቶችን እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ትስስር እንዲሁም አብሮ የመሥራት እንቅስቃሴን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በመድረኩ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የተውጣጡ ወጣት ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በቀጣይ በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ከወጣቶች የሚጠበቁ ተግባራት ላይ እና የሚኖራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!