
ባሕር ዳር: ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝቡን የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎቶች ለማሟላት በበጀት ዓመቱ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አዲስ የመንገድ ግንባታ እና የድልድይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንገድ መምሪያ ኀላፊ ጥላሁን እሽቴ ገልጸዋል።
የኅብረተሰቡን የመንገድ ፍላጎት ለማሟላት በበጀት ዓመቱ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አንድ ኮንክሪት እና ሁለት ተንጠልጣይ ድልድዮች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል። ድልድዮቹ የተገነቡት በዚገም፣ በአየሁ ጓጉሳ አና በባንጃ ወረዳዎች ነው። በዚህም ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ማድረጉን ኀላፊ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የተጀመሩ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሁለት ድልድዮችም በበጀት ዓመቱ ስለመጠናቀቃቸው ነው የተብራራው። በበጀት ዓመቱ 39 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ የጥገና ሥራ ስለመከናወኑም ነው የተገለጸው፡፡ 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አዲስ የመንገድ ሥራ በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በአንከሻ፣ በጓንጓ እና በባንጃ ወረዳዎች ማከናወን ተችሏል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአማራ ክልል መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ 109 ኪሎ ሜትር ጥገና መደረጉን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን ለአብነት በአንከሻ ወረዳ የብዙ ጊዜ ጥያቄ የነበረው ከበካፍታ መሰላ እና በባንጃ ወረዳ ከእንጅባራ ጉባላ ያለው መንገድ ችግር ስለመፈታቱም ነው ያብራሩት።
ኅብረተሰቡ የተሠሩ መንገዶችን ዘላቂ በማድረግ ረገድ ባለቤት እየኾነ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን እንዳለው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንገድ ሽፋን 74 በመቶ መድረሱን የገለጹት አቶ ጥላሁን ከኅብረተሰቡ የመልማት ፍላጎት አንፃር ገና መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!