የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀልን ለመከላከል በአሽከርካሪዎች እና ቤት አከራዮች ላይ ልዩ ደንብ አወጣ።

11

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የከተማውን ሰላም እና ደኅንነት ለማስከበር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል ክልከላዎችን በአሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እና በቤት አከራዮች ላይ ገደብ አስቀምጧል።
መምሪያው ለአሚኮ በላከው መግለጫ ባለ ሶስት እግር የባጃጅ እና ፎርስ አሽከርካሪዎች ፊብሪካው ከሠራው ስሪት ውጭ መጋረጃ ፣ በር እና የተለያዩ አልባሳትን በመጠቀም ወንጀል ለመፈፀም እና ዕይታን ለመጋረድ የሚያስችሉ ማንኛውንም ነገሮች መጠቀም እንደማይቻል ገልጿል ።

ሁሉም አሽከርካሪዎች ሁለቱንም ሰሌዳ ሳያስሩ እና አንድ ሰሌዳ ብቻ አስሮ ማሽከርከር ፣የታክሲ አገልግሎት መርሃ ግብር ሳይኖራቸው ማሽከርከር ፍጹም የተከለከለ መሆኑን እና የማኅበሩ መለያ የያዘ እና በስቲከር የተጻፈ መለያ ቁጥር ጋር ከርቀት የሚታይ በመለጠፍ ሕግ አክብረው በትኩረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጿል ።

በከተማዋ አሥተዳደር ውስጥ ማንኛውም አሽከርካሪ ከምሽት 1:00 እስከ ንጋት 12:00 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑን መምሪያው አሳውቋል ። ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራዮችን ሙሉ አድራሻን መታወቂያ ፎቶ ኮፒ በማድረግ በክፍለ ከተማው ለሚገኙ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች በአካል በመቅረብ ማስመዝገብ እንዳለባቸው አሳስቧል።

ኅብረተሰቡ የከተማውን ሰላም እና ደኅንነት ለማስከበር ሲባል ከመቼውም በበለጠ አካባቢውን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ እና ጸጉረ ልውጥ እና አጠራጣሪ ኹኔታዎች ሲያጋጥሙ በየአካባቢው ከሚገኙ የጸጥታ ኀይሎች ጋር በቅንጅት እንዲሠራ የጸጥታ ምክር ቤቱ አሳስቧል ። በዝርዝር የተቀመጡ ክልከላዎችን በማያከብሩ እና ተላልፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ፣የቤት አከራዮች እና ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ መምሪያው በአንክሮት ገልጿል ።

ከዚህ በፊት በከተማው የሚገኙ የጸጥታ ኀይሎች በጋራ ባከናወኑት ተግባር ከሕግ ውጭ በከተማ ውስጥ መርሃ ግብር ሳይኖራቸው አገልግሎት የሚሰጡ ፣ሰሌዳ ሳያሟሉ የሚያሽከረክሩ ከወንጀል ድርጊት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን እና ከአቅራቢያ ወረዳ እና ዞኖች የመጡ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ወደ መጡበት እንዲመለሡ መደረጉ ተገልጿል ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲሠሩ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
Next articleየመንገድ መሠረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ፡፡