ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲሠሩ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

57

ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ጎንደር ዞን ሁሉም ወረዳዎች ሕዝባዊ የሠላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

በሰላም ኮንፈረንሱ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ማስፈን የሁሉም አካላት ድርሻ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲፈጸሙ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡

በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አስተዳዳሪ መሉ አበጀ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፣ ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት እና የልማት ሥራዎችን መከወን አይቻልም ብለዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም መስፈን ከፍተኛ ዋጋ እንዳለቸው የተናገሩት አስተዳደሪው በየአካባቢያቸው ነፍጥ አንግበው ከመንግሥት ጋር ውጊያ እያደረጉ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለውይይት እንዲቀርቡ እና ጥያቄዎች በሰላም እንዲፈታ የበኩላቸውን ድረሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ወይዘሮ አምሳል ተስፋ እንደ አማራ ወደ ነበርንበት ልማት ለመመለስ ሰላም ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ አንድ ኾነን መፍትሔ ማምጣት ይገባናል ያሉት ኅላፊዋ የአማራ ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉት በጠመንጃ ሳይኾን በጠረንጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኩታ ገጠም እርሻ ሥራው በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያሳካ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀልን ለመከላከል በአሽከርካሪዎች እና ቤት አከራዮች ላይ ልዩ ደንብ አወጣ።