በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር መድረክ ተካሄደ።

29

ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመርሐ ግብሩ ከከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በጎ ፍቃደኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ወጣት አካልነው አስማረ እና እፁብ ድንቅ ጥላሁን በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሦስት ዓመታት ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዛሬም በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በተካሄደው የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተሳታፊዎች ናቸው።
ተሳታፊዎቹ በጎ ፈቃድ ለሌሎች ከመትረፍ ባለፈ ለራስ የሚሰጠው ደስታ ከፍ ያለ ስለመኾኑ ነግረውናል።

በጎነት ለራስ ነው የሚሉት በጎ ፈቃደኞቹ የበጎ ፈቃድ ሥራ ተሳትፏቸውን አጠናክረው በያዝነው የክረምት ወራት በልዩ ልዩ ዘርፎች ተሳትፎ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማሩ መሐመድ በከተማዋ በክረምት በጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በ14 ዘርፎች በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ150 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በጎነት ለበርካቶች መድረስ የሚያስችል መኾኑን ገልፀው በከተማ አሥተዳደሩ በበጎ ፈቃደኝነት መልካም ተግባርን እየሠሩ ያሉ ወጣቶች እና ማኅበራት መኖራቸውን አብራርተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎነትን እና አጋርነትን የሚሻ በመኾኑ ለውጤታማነቱ የሁሉንም ማኅበረሰብ ተሳትፎን የሚጠይቅ ስለመኾኑ በመድረኩ ተገልጿል።

ዘጋቢ-ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ በሰቆጣ ከተማ ለተቸገሩ ወገኖች የሚውል 560 ኩንታል ማሽላ ድጋፍ አደረጉ።
Next article“የኩታ ገጠም እርሻ ሥራው በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያሳካ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)