የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ በሰቆጣ ከተማ ለተቸገሩ ወገኖች የሚውል 560 ኩንታል ማሽላ ድጋፍ አደረጉ።

40

ሰቆጣ: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አቡነ በርናባስ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ለሚኖሩ እና የተቸገሩ ወገኖች የሚውል 560 ኩንታል ማሽላ ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መይትወ ወርቁ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ተቸግረው እንደነበር አውስተው ስለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የተደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ የቤተሰቦቻቸውን ችግር የሚቀርፍ እንደኾነ የተናገሩት ወይዘሮ አለም ጀጃው ለክረምቱ የሚኾን ቀለብ ካገኙ ጠንክረው ሠርተው ለመለወጥ መነሻ እንደሚኾናቸው ጠቁመዋል። ድጋፉን ያበረከቱት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርናባስ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ወገኖች በተገኘ 3 ሚሊየን 117 ሺህ ብር ወጭ 560 ኩንታል የማሽላ እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከአሁን በፊትም በሰሃላ ሰየምት፣ በዝቋላ፣ በአብርገሌ ወረዳ እና በሰቆጣ ከተማ ለሚኖሩ ወገኖች ከ2 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ያወሱት አቡነ በርናባስ ድጋፉን ላበረከቱት በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል። የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መላሽ ወርቃለም በበኩላቸው የተበረከተው 560 ኩንታል እህል ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ 3 ሺህ 600 የከተማው ማኅበረሰብ ክፍሎች የወር ቀለብ እንደሚኾን ገልጸዋል።

ከንቲባ መላሽ ወርቃለም አቡነ በርናባስ ለጤና ተቋማት፣ ለተቸገሩ ወገኖች፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች እና በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ላበረከቱት አስተዋጽኦ በከተማው ሕዝብ ስም አመስግነዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምርያ ኅላፊ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው ብፁዕ አቡነ በርናባስ ሕዝባችን ያለበትን ውስብስብ ችግሮች ለማቃለል በጎ አካላትን በማስተባበር ላደረጉት ድጋፍ አመሰግነው የብሔረሰብ አስተዳደሩ ማኅበረሰብ በእርዳታ የተቀየረ አካባቢ አለመኖሩን በመረዳት ሁሉም ለልማት ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

የብሔረሰብ አሰተዳደሩ የአካባቢውን ጸጋዎች በመጠቀም ማኅበረሰቡን በምግብ እህል ራሱን እንዲችል እየሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ሹመት ከተረጅነት መንፈስ ለመላቀቅ መጪውን ክረምት እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበርካታ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸው ተገለጸ።
Next articleበጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር መድረክ ተካሄደ።