በርካታ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸው ተገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ.ር) ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን ተናገረዋል።

ኢትዮጵያን ከተረጂነት ማላቀቅ የብሔራዊ ክብር ጉዳይ በመኾኑ ለተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ.ር) እንደገለጹት ሀገርን ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችል የቅድመ-አደጋ መከላከል፣ የአደጋ ወቅት እና ከአደጋ በኋላ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሠራር እየተዘረጋ ነው።

ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎችም በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄድ የዳሰሳ ጥናት ተጋላጭነትን ማሥቀረት የሚያስችል የልማታዊ ሴፍቲኔት ድጋፍ ሥርዓት እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ረጂ ድርጅቶችም የዕለት ደራሽ ድጋፍ መስጠት ሰብዓዊነት ቢኾንም ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በዘላቂ የልማት ግብ ተሠማርተው ተረጂዎች እራሳቸውን በሚያቋቁሙበት የሥራ መስክ መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ግጭት ለነበረባቸው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ድጋፍ እየቀረበ መኾኑን ጠቁመው በቀጣይም ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን እንዲችሉ ይደረጋል ብለዋል። ኢትዮጵያን የሚመጥን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በመቅረጽ የአደጋ መከላከል እና መቆጣጠር እንዲሁም የፈንድ እና ክምችት አቅምን ማጎልበት የሚያስችሉ አሠራሮች እየተዘረጉ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ፅንፈኞች ጀግና አመራሮችን በመግደል፣ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት አይችሉም” ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ በሰቆጣ ከተማ ለተቸገሩ ወገኖች የሚውል 560 ኩንታል ማሽላ ድጋፍ አደረጉ።