
ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች በኬሚሴ ከተማ ከሕዝብ ጋር ተወያዩ።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ አሊ ህልፈተ ሕይዎትን ተከትሎ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በማስመልከት ከብሔረሰቡ አስተዳደሩ መሪዎች፣ የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ምክክር አድርገዋል። በምክክር መድረኩ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚዳስስ የመነሻ ሰነድ ቀርቧል። መነሻ ሰነዱን መሠረት አድርገውም ውይይት ተካሂዷል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር መንግሥት እና ፓርቲ የጣሉበትን ሕዝባዊ ኀላፊነት እየተሻሻለ መምጣቱ በበጎ ጎን ተነስቷል። በተለይ ለጋራ ዓላማ በጋራ በመቆም የሕዝብን ደህንነት ከማረጋገጥ ረገድ ተቀናጅቶ እና ተናብቦ መሥራት ላይ የተሻለ ርቀት ተሂጇል ብለዋል። የአመራሩ ኀላፊነት እና ተልዕኮ ተቀብሎ የመሥራት ባህል እየተሻሻለ ቢመጣም ሁሉም አመራር እኩል አለመጨነቅ እና አለመንቀሳቀስ ክፍተት እየፈጠረ እና ውስኖችን ለመስዋዕትነት እያዳረገ መኾኑ ተነስቷል።
የዞን እና የወረዳ አመራሮች የተጣለባቸውን ኀላፊነት በብቃት አለመወጣታቸውን በመግለፅ በቀጣይ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም የተሻለ ለመሥራት በተለይ የሕዝብን ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል ምክክር ተካሂዷል። ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “ፅንፈኞች ጀግና አመራሮችን በመግደል የሥርዓት ለውጥ ማምጣትም ይሁን ጀግኖች የተሰውለትን ዓላማ ከማሳካት ለማስቆም አይችሉም” ብለዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተጠቃሚነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሪዎች ኀላፊነታቸውን በብቃት መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው ፅንፈኞች ከኔ በላይ ላሳር የሚሉ፣ ሕዝብን ኾደ ባሻ በማድረግ ለሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ተወሽቀው ለተለያዩ የጥፋት ኃይሎች የሚላላኩ የሀገር ህመም ሁነዋል ብለዋል። የተጀመረውን የተደራጀ ትግል አጠናክሮ በማስቀጠል ሽንፈታቸውን ማፋጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የምንፈልጋትን ሀገር ለመገንባት አመራሩ ጠንካራ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል ያሉት አቶ ይርጋ በመርህ የሚመራ እና የዓላማ ፅናት ያለው መሪ መኾን ይጠበቅብናል ብለዋል። እንደ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ ውይይቱ የቀጣይ ጊዜ ተግባራትን የሚመለከት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቅቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!