
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ በኩል የክልሉ የሰላም ካውንስል ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንሚደግፋ እና ለተፈጻሚነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ሠራተኞች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገረዋል። የወረዳው የሀገር ሽማግሌ ሃምሳ አለቃ ንጉሴ ጎባለ እያጋጠመ ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
አሁን ያለው ሰላም ነገም በአስተማማኝ ደረጃ ሊቀጥል የሚችለው ሁሉም ለሰላም ሲሠራ እና ሰላምን የሚያፈርሱ ነገሮችን ያለ ምህረት ሲታገል ብቻ ነው ሲሉ መናገራቸውንም የዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል። ኅብረተሰቡ ያለስጋት እንዲንቀሳቀስ እንዲሁም ሕዝብ እና መንግሥት የበለጠ ተናብበው ልማቱን ማሳለጥ እንዲቻል በጫካ ያሉ ወንድሞቻችን የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በትኩረት እንዲያዩት አሳስበዋል።
በዞኑ የመንግሥት ሠራተኛ የኾኑት ወይዘሮ ፀሐይነሽ ሻውል የሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ችግሮችን በውይይት እና በሠለጠነ መንገድ መፍታት ይገባል ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ የመንግሥት ሠራተኛ አቶ ሐሰን አልቃሲም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም የጸና አቋም በመያዝ መንቀሳቀስ ይኖርብናል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!