
ባሕር ዳር: ሀምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሕዝብ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ዋናው የመሠረተ ልማት ጥያቄ ነው። ከዚህ መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት አንዱ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት እና ጠለምት ወረዳ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለረዥም ጊዜ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የድልድይ ግንባታ ይጠቀሳል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ የአዲምረት ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ክብረት አይንሸት እና አቶ አራጋው እንዳለው በቀበሌያቸው መሐል አቋርጦ የሚያልፍ ወንዝ እንደነበር እና በክረምት ወቅት ነፍሰጡር እናቶች እና የህክምና አገልግሎት የሚሹ ታካሚዎች በወቅቱ ለህክምና መድረስ ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ ምርታቸውን በሰዓቱ ጠብቀው ለገበያ እንደማያቀርቡ እና ወንዙ የብዙ ሰዎች እና እንስሳትን ሕይወት ይቀጥፍ እንደነበር ገልጸውልናል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ድልድዩን ከሠራላቸው በኋላ የነበሩባቸው ችግሮች ተቀርፈው ኅብረተሰቡ እንደልቡ መንቀሳቀስ እንደጀመረ እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሽተኞች እና ነፍሰጡር እናቶች ወደ ህክምና ለመሄድ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን እና የተመረቱ ምርቶች ወቅቱን ጠብቀው ለገበያ ማቅረብ ስለመቻላቸው ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡ በክረምት ወቅት የሰው እና እንስሳት ሕይወት መቀጠፍ ታሪክ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የዲዛይን እና ኮንስትራክሽን ዳይሬክተር ኤርሚያስ መኮንን ክልሉ በሁሉን ዓቀፍ የመንገድ ተደራሽነት ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል ከ12 ሜትር በላይ የኾኑ የተዘለሉ ከፍተኛ ድልድዮች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ በጭራ ቀበሌ በ25 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጭ 22 ሜትር ርዝመት እና 8 ነጥብ 1 ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ ተሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። ድልድዩ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ሲኾን እስከ 50 ዓመት ድረስ ያገለግላል ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች 270 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራ በዕቅድ ተይዞ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና በወረዳ በጀት ወደ 250 ኪሎ ሜትር ተሠርቷል። ከሐምሌ1/2015 ዓ.ም ጀምሮ 24 ተንጠልጣይ ድልድዮች እና 13 የኮንክሪት ድልድዮችን በዕቅድ ይዞ ሁሉም በሚባል ደረጃ ተጠናቅቀው የምረቃ እና ለአገልግሎት ክፍት የማድረግ ሥራ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል።
በሥራቸው ወቅት በወቅታዊ ሁኔታው ምክንያት ባለሃብቶች ማሽኖችን የማቅረብ ፍላጎት ያለመኖር፣ የመንገድ መዘጋት፣ የነዳጅ በወቅቱ ያለማግኘት እና የግንባታ ግብዓቶች በየጊዜው ዋጋ መጨመር ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልጸውልናል። ለቀጣይ ከዚህ በፊት ሁሉን አቀፍ የመንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም የነበረው የገጠር መንገዶች ትስስር ለምግብ ዋስትና በሚል ወርልድ ባንክ 70 በመቶ ክልሉ ደግሞ 30 በመቶ በያዙት በጀት የመንገድ ግንባታ ሥራ፣ የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ እና የኮንክሪት ድልድይ፣ የጥገና ሥራ እና ልዩ ልዩ ስትራክቸሮችን ለመሥራት በዕቅድ እንደተያዘ ተናግረዋል።
የተሠሩ መንገዶችን እና ድልድዮችን ማኅበረሰቡ ከጉዳት መጠበቅ እንደሚኖርበት እና በየመንገዶቹ ችግኝ እንዲተክልም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!