
ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ የሰላም ኮንፈረንሶች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
በአማራ ክልል በበርካታ አካባቢዎች የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ መኾኑን አሚኮ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል፡፡ እየተካሄደ ያለው የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬም ሲቀጥል በሰሜን ጎጃም ዞን አዴት ከተማ፣ በደቡብ ወሎ ዞን ለገሂዳ ወረዳ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነባሩ ጭልጋ ወረዳዎች የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በሰሜን ጎጃም ዞን በአዴት ከተማ አስተዳደር “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ የመንግሥት ሠራተኞች የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በመደረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዴት ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ንብረት አበጀ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው፣ ሰላም ከሌለ ራስን ቤተሰብን እና ሕዝብን መምራት፣ ሰርቶ መብላትም ኾነ ወጥቶ መግባት አይቻልም ብለዋል።
ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተፈጠረው ግጭት በከተማዋ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እጅግ የከፋ ነበር ተብሏል፡፡ ከዚህም ለመውጣት በተከፈለው መስዋዕትነት አሁን ላይ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማፅናት የመንግሥት ሠራተኞች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ለገሂዳ ወረዳ “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የመንግሥት ሰራተኞች የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በኮንፈረንሱ መልእክት ያስተላለፉት የለገሂዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሙሳ ተገኝ የአማራ ክልል የገጠመውን ውስብስብ ችግር መውጣት የሚቻለው በመወያየት እና መፍትሄ በማስቀመጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የኮንፈረንሱ ዓላማም ለችግሮች መፍትሔ ለማመንጨት መኾኑን ነው ያመለካቱት፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በነባሩ ጭልጋ ወረዳ መንግሥት ሰራተኞች ጋር የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በነባሩ ጭልጋ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል ከጠቅላላ መንግሥት ሰራተኞች ጋር የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ መኾኑን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!