“ምክር ቤቶች የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን የመቆጣጠር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለባቸው” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

18

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየዓመቱ የሚካሄደው የፓርላማ ጥናት እና ምርምር ኮንፈረንስ ዛሬ ለ4ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ኮንፈረንሱ “የኢትዮጵያ ፖርላማ ለሕዝብ ጥቅም እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። በኮንፍረንሱ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት የክልል እና የከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤዎች፣ ሚንስትሮች፣ የቀድሞ የምክር ቤቱ አመራሮች ፣ የተጠሪ ተቋማት ኅላፊዎች፣ ምሁራን እና የዩኒቨርስቲ ኘሬዚዳንቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቶች የሕዝብ ውክልና እና ሉዓላዊነት የሚረጋገጥባቸው የዲሞክራሲ ተቋማት መኾናቸውን ገልጸዋል። አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ “ምክር ቤቶች የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን የመቆጣጠር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለባቸው” ብለዋል።

ኮንፈረንሱ ምክር ቤቶች ሥራቸውን በጥናት እና ምርምር የተደገፈ እና ሳይንሳዊ መንገድን የተከተሉ መፍትሔዎችን ለማቅረብ ያለመ መኾኑን ገልጸዋል። አስካሁን የተደረጉ ጥናት እና ምርምሮች ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ እና 4ኛው ኮንፈረንስ ጠቃሚ እና ገንቢ ሀሳቦች የሚገኙበት ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ምክር ቤቱ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ለዲጂታል ዘርፉ ፈተናዎች ምላሽ መስጠት የሚችሉ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወንበረማ የመንግሥት ሰራተኞች የወረዳቸውን ሰላም ለመመለስ ድርሻችን ከፍተኛውን ነው አሉ።
Next articleበምስራቅ ጎጃም ዞን 24 የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደሮች ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።