
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በክልላችን ለወራት የዘለቀው የሰላም እና የፀጥታ ችግር ለመጨረሻ ጊዜ በድርድር እንዲቋጭ በክልሉ መንግሥት የተላለፈውን የሰላም ጥሪ ዳር ለማድረስ ሁሉም ማኅበረሰብ በየደረጃው የጋራ ምክክር በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በከተማችን ባሕር ዳር የሁሉም ትምህርት ቤት መምህራን ፣ርእሳነ መምህራን ፣ሱፐርቫይዘሮችና ሌሎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።
በዚህም የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የክፍለ ከተማ ደጋፊ አመራሮች ፣የክፍለ ከተማ አመራሮች እንዲሁም መምህራን ፣ርእሳነ መምህራን ፣ሱፐርቫይዘሮች በምክክር መድረኩ ተገኝተዋል። በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የሚያስችል የጋራ መድረክ በማመቻቸት፣ ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ በመስጠት ሕዝቡን ከተጨማሪ ቀውስና ጉዳት ለማዳን የተዘረጋውን የሰላም ጥሪ ለመልካም ትውልድ ግንባታ ቀዳሚ ባለድርሻ እንደመሆናቸው መጠን አሁን ለገጠመው ችግር የመፍትሄ አካል በመሆን የተጀመረውን ሰላም የመፍጠር ተግባር በመደገፍ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።
የከተማ አሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመላክተው መምህራን እንደ ክልልም ይሁን እንደ ሀገር ያጋጠሙ ፈተናዎችን በፅናት ለማለፍ እና ሕዝቡን ወደ ሰላምና ልማት ለማሻገር የችግሮቹን መነሻ በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተገቢ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ለቀጣይ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ጤናማነት መረጋገጥ አተኩረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በቀረበው የመወያያ ጽሁፍ ተብራርቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!