“በክልሉ የሰላም ካውንስል የቀረበው የሰላም አማራጭ እና የድርድር ሀሳብ ሰላምን ለማረጋገጥ እድል የሚፈጥር ነው” የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች

22

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ሥር ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች እና በከተማ አሥተዳደሮች ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረስ ተካሂዷል። በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ እና መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር፣ መተማ እና አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳዎች በተለያዩ ቀበሌዎች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሰላም ኮንፈረንሱ የተካሄደው።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እያሳደረባቸው መኾኑን የኮንፈረሱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ንጹሀንን ለህልፈት ዳርጓል፤ የሕዝቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር እንዲቋረጥ፣ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ፣ እገታ፣ ዘረፋ እና ሌሎች ሕገ ወጥ ወንጀሎች እንዲበራከቱ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በክልሉ የሰላም ካውንስል የቀረበው የሰላም አማራጭና የድርድር ሀሳብ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚቀርፍ እና ሰላምን ለማረጋገጥ እድል የሚፈጥር መኾኑንም ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት። በመኾኑም የታጠቁ ኃይሎች ጥያቄዎቻቸውን በሠለጠነ እና ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲፈቱ የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን የመፍትሔ አማራጭ መቀበል አለባቸው ብለዋል።

ከትጥቅ ትግል ይልቅ ችግሮችን በድርድር እና በውይይት በመፍታት የክልሉን ሕዝብ አሁን ካለበት ስቃይ እና እንግልት ሊታደጉት እንደሚገባም አሳስበዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት ሁሉም ለሰላም መስፈን አበክሮ ሊሠራ እንደሚገባም ተመላክቷል።

በኮንፈረንሱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአራት ኪሎ-ቀበና-ኬንያ ኤምባሲ ኮሪደር ሥራ ተጠናቅቋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበባሕር ዳር ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የመምህራን የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ።