“አሕመድ አሊ ፅንፈኝነትን በሀቅ እና እውነት ላይ ኾኖ የሞገተ ጀግና፤ ለሕዝብ አብሮነት ከልብ የሠራ እውነተኛ መሪ ነበር” ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

146

ባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በአማራ ክልል የብልፅግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮነን፣ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እና የኮምቦልቻ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ህልፈተ ሕይዎት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በከሚሴ ከተማ ተገኝተው ገልጸዋል።

መሪዎቹ የክልሉን መንግሥት በመወከል የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለመግለፅ በከሚሴ ከተማ ተገኝተው የአቶ አሕመድ አሊ ቤተሰቦችን በማጽናናት በመቃብሩ ላይ የክብር የአበባ ጉንኑን አስቀምጠዋል።

አቶ አህመድ አሊ በሕይዎት ዘመኑ እውነተኛ፣ ሀቀኛ እንዲሁም ለሚመራው ሕዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሌት ከቀን የዞኑን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ ሲደክም የነበረ ወንድማችን ነበር ያሉት መሪዎቹ አሻራው ለዘላለም ሲታወስ የሚኖር የሕዝብ ልጅ ነው ብለዋል።
መሪዎቹ ለቤተሰቡ እና ወዳጅ ዘመዶቹ፤ ለሥራ ባልደረቦቹ እና ለመላው የኦሮሞ ብሔረሰሰብ አስሀዳደር ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “አሕመድ አሊ ፅንፈኝነትን በሀቅ እና እውነት ላይ ኾኖ የሞገተ ጀግና፤ ለሕዝብ አብሮነት ከልብ የሠራ እውነተኛ መሪ ነበር” ብለዋል።

በመጨረሻም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የአቶ አሕመድ አሊን ቤተሰቦች ለመደገፍ ቃል መግባቱን ገልጸው፤ በዋና አስተዳዳሪው ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያ አውግዘዋል።

በሃዘን መግለጫ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ሽማግሌዎች የፅንፈኞች ሴራ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሕዝብ ለዘመናት ይዞት የዘለቀውን አብሮነት ለመሸርሸር የተደረገ ጥረት ነው ብለዋል።

ድርጊቱ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ሕዝብ እና መንግሥት መናቅ ነው ያሉት ሽማግሌዎቹ መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች በመለየት ለሕግ እንዲያቀርባቸው መጠየቃቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳር: ሐምሌ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ስር ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር ትናንት ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረስ ተካሂዷል።
Next article“የአራት ኪሎ-ቀበና-ኬንያ ኤምባሲ ኮሪደር ሥራ ተጠናቅቋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)