
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት በተሠሩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ እና በቀጣይ በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል የመንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ለውይይት መነሻ የሚኾን ጹሑፍ አቅርበዋል።
ባቀረቡት ጹሑፍ እንዳሉት ቢሮው በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ መንግሥት፣ በወረዳ አሥተዳደር ምክር ቤት የበጀት ድጋፍ እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ 363 ኪሎ ሜትር አዲስ የመንገድ ግንባታ ሥራ አቅዶ 352 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባት ችሏል።
በሌላ በኩል በክልሉ መንግሥት በጀት 17 የኮንክሪት ድልድዮችን በቢሮው፣ 31 ድልድዮችን በገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ እና 24 ተንጠልጣይ የእግረኛ ድልድዬችን በሄልቬታስ ኢትዮጵያ ቅንጅት በመገንባት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
በበጀት ዓመቱ የመንገድ ዘርፋ አፈፃፃም በጥራት፣ በብቃት፣ በተደራሽነት እና በታቀደለት በጀት ልክ በመሠራት ላይ እንደሚገኝም ነው የተብራራው።
በክልሉ በጀት በገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ 89 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር፣ በወረዳ አሥተዳደር ምክር ቤት በጀት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ በቅንጅት 263 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር በጥቅሉ 352 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ስለመሠራቱ ተገልጿል።
ቀደም ሲል የተገነቡ 11 ሺህ 668 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተሠርተዋል ተብሏል።
በሁሉም ዘርፎች ወደ ሥራ በገቡ 523 ፕሮጀክቶች 27 ሺህ 939 ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፈጠሩ በላይ የቴክኖሎጅ ሽግግር እና የሥራ ባሕል ማደጉ ተነስቷል።
በተገነቡ መንገዶች 109 ቀበሌዎች መተሳሠራቸው ትልቅ ሥራ በመኾኑ በቀጣይ የበለጠ ማስፋት እንደሚገባ ተመላክቷል።
የሕዝቡን አቅም በመጠቀም ከ797 ሚሊዮን 329 ሺህ 219 ብር በላይ በማሠባሠብ ለመንገድ ግንባታ እና ጥገና ሥራዎች እንዲውል መደረጉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው የተገለጸው።
ለመንገድ ዘርፉ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከመከታተል እስከ መደገፍ እንዲሁም የሦስትዮሽ ውይይቶችን በማድረጉ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር ማስቻሉን ነው ዶክተር ጋሻው የተናገሩት።
ቢሮ ኀላፊው “በክልሉ ፕሮጀክትን በውጤታማነት የመምራት ባሕል ተቋማዊ እንዲኾንም የሕዝብ እንደራሴዎች ሚና ከፍተኛ ነወ” ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ለቀጣይ በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት በመስጠት ማጠናቀቅ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴዎቹ አሳስበዋል።
ለተፈፃሚነቱም በየደረጃው ያለ መሪ እና ሠራተኛ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም ነው ያስገነዘቡት።
በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች፣ የመንገድ ቢሮ እና የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ መሪዎች እና የርእሰ መሥተዳድሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
