
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ፋሲሎ እና አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ቀበሌዎች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉበት የሰላም ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ወንድሙ የተባሉ የዕድሜ ባለጸጋ “በአማራ ክልል በሁሉም አቅጣጫዎች በሰላም እጦት ምክንያት ህሙማን እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው መታከም ባለመቻላቸው ሕይዎት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው” ብለዋል።
አቶ ወንድሙ ጨምረው እንደተናገሩት የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች በሰላም ተንቀሳቅሰው ያመረቱትን መሸጥ ብሎም መሸመት ባለመቻላቸው ከመቸውም በላይ የኑሮ ውድነቱ ጨምሯል፤ ማኀበራዊ መስተጋብሮች ኹሉ ተስተጓጉለዋል ብለዋል። ታዲያ ይህ መሰሉ ችግር የሚወገደው ሰላም ሲኖር ነው። በመኾኑም ሁሉም ሰው ለሰላም መስፈን በቅንነት ሊሠራ ይገባዋል ነው ያሉት።
ሌላው የሰላም ውይይት ተሳታፊ አቶ የሺዋስ እንዳሉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአማራ ክልል ሰላም በመጥፋቱ የተማሪዎች ውድ የትምህርት ጊዜ ባክኗል።
አርሶ አደሮችም በሰላም እጦት የተነሳ መሬታቸውን በአግባቡ ማረስ ካለመቻላቸው በተጨማሪ ግብዓት በፈለጉበት ሰዓት እና ወቅት ገዝተው ለመጠቀም መቸገራቸውን ጠቁመዋል።
ስለኾነም ይህ የሰላም እጦት በቀጣይ የሰብል ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። እናም እርስ በእርስ በመተሳሰብ ጊዜው ቢረፍድም ሳይመሽ ለሰላም መስፈን መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል።
አቶ መሐመድ የተባሉ መምህር በበኩላቸው ሰላም አዋኪዎችም ኾነ የሰላም ዘቦች እኛው ስለኾንን ሁላችንም በየቤታችን መምከር ይገባናል። ጥያቄን በጠመንጃ ሳይኾን በሠለጠነ መንገድ በማቅረብ ቁርሾን ለትውልድ በማያሻግር መልኩ ማምከን ይኖርብናል ነው ያሉት።
መምህር መሐመድ “ሥውር ተልዕኮ ያላቸውን ከፋፋይ የሴራ ፖለቲካ ደላሎችን መንጥረን በመለየት ሰላማችንን በማስፈን ልናተርፍ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል። ተጽዕኖ ፈጣሪ የሃይማኖት አባቶችን በየቤተ ዕምነታቸው ልጆቻቸው ለሰላም አብረው እንዲነሱ ሰርክ ሊያስተምሩ እና ሊገስጹም ይገባል ብለዋል።
ወይዘሮ መዓዛ የተባሉ የሰላም ውይይቱ ተሳታፊ ሰላም በመጥፋቱ ሠርተን እንዳንበላ ኾነናል ነው ያሉት። በየቀኑም የሰው ልጅ ሃብት ንብረቱን ከማጣቱ ባለፈ ሕይዎት እንደ ጤዛ እየረገፈ ነው፤ ስለዚህ በግጭቱ እና በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች ሁሉ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመወያየት ጥያቄን በሰላም ማስመለስ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ገረመው አባተ እንዳሉት የሰላም ጉዳይ ቦታ፣ ፆታ፣ ዕድሜ እና ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉንም ይነካል። በመኾኑም ኀብረተሰቡ “ሞት ይበቃናል! መገዳደል ይብቃ” ብሎ መፍትሔ አመላካች ውይይት በማድረግ አንዱ ለሁሉም ሁሉም ለአንዱ ሰላም መስፈን ለመሥራት ተግባብቷል ብለዋል።
ዋና ሥራ አሥፈጻሚው መንግሥት የሰላም ጥሪው ውጤታማ እንዲኾን ትኩረት አድርጎ መሥራት አንዳለበትም ተወያዮች አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል ነው ያሉት።
በዛሬው “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” ውይይት ኀብረተሰቡ ለሰላም መስፈን የሚጠበቅበትን ለማድረግ ቃል መግባቱን ነው አቶ ገረመው የተናገሩት።
መሳሪያ ይዘው ጫካ በመግባት በጦርነቱ እና በግጭቱ እየተሳተፉ የሚገኙት ወንድም እና እህቶቻችን ጥያቄያቸውን በሚፈልጉት መልኩ በሰላማዊ መንገድ እውን ለማድረግ ወደ ጠረጴዛ መጥተው የውይይቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ኀብረተሰቡ መጠየቁን ነው አቶ ገረመው ያብራሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
