
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልላችን ያለውን የሰላም ችግር በውይይት በንግግርና በድርድር ለመፍታት በፋር ጣ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል። በኮንፈረንሱ በእግር መትከል ምዕራፍ የተሠሩ ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር እና በቀጣይ ተልዕኮ የሚሰጥባቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እና በመሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ተደርጓል።
ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደሰላም መምጣት እንዳለባቸው የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ባለመሥራቱ ሕዝቡ ለዘረፋና ለስርቆት እየተዳረገ መኾኑም ተነስቷል።
የተፈጠረውን የሠላም መደፍረስ ችግር አሁንም በውይይትና በድርድር መፈታት እንዳለበት፣ ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ችግር ወጥታ ልማት በማልማት ሕዝቦቿን ተጠቀሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ።
መንግሥት ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንዳለበት፣ በክልላችን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመልካም አሥተዳደርና የልማት ሥራዎችን በዕቅዳቸው መሠረት መፈጸም አለባቸው ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን ለመፍታት መንግሥት ትኩረት መስጠት የተናገሩት ተሳታፊዎ በፀጥታ ምክንያት የጤና አገልግሎትንና የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን በማዘመን ረገድ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል። ተሳታፊዎቹም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ነው የተናገሩት።
ለሰላም ሲባል መንግሥት የሠላም ጥሪ ማድረጉ ለሰላም ያለዉ ፍላጎት የሚደነቅ በመኾኑም ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ክልል የገጠመን የሠላም መደፍረስ ክልላችን በእጅጉ የጎዳና ከልማት ጉዞ ያደናቀፈን እንደሆነ ተወስዶ ይህም በአንድ አካል ብቻ የማይሠራ በመኾኑ ለሠላምና ለልማት ሁሉም መታገልና አርበኛ መኾን እንዳለበት በማስገንዘብ መግባባት መቻሉን ከዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኮንፈረንሱም በቀጣይም ለልዩ ልዩ የኅብረተሠብ ክፍሎች፣ ለሴቶች፣ ለመምህራን፣ ለንግዱ ማኅበረሰብ፣ ለሃይማኖት አባቶችና ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለወጣቶችና ለመንግሥት ሠራተኞች በወረዳ ደረጃ የሚቀጥል መኾኑ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
