
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ድርቅ እየተከሰተ በርካቶችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፤ የሰው ሕይዎት አጥፍቷል፤ እንስሳትንም ጎድቷል፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን ረሀብ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም ሕዝብ ባለማሳወቁ እና እርዳታ ከለጋሾች ባለመጠየቁ መትረፍ የነበረባቸው ወገኖች ሕይዎት በከንቱ ተቀስፏል፡፡ ከዚህ እሳቤ ተነስቶም የቢቢሲው ጋዜጠኛ ዲምብልቢ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ረሀብ “ድብቁ ረሀብ” በማለት ነበር የገለጸው፡፡ መቅሰፍቱ ከበሽታ ጋር ተጨምሮም 100 ሺህ ያህል ሰው እንደገደለ ነው ጋዜጠኛ ዲምብልቢ የዘገበው፡፡
ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ድርቅ እያስከተለ ያለውን የሰው ሕይዎት መቅሰፍት ለመታደግ እርዳታ ማሠባሠብ አይነተኛ መፍትሔ መኾኑንም ተናግሯል፡፡ ድርቁ እና ረሀቡ ያሳደሩት ኪሳራ ቁጭት ውስጥ ያስገባቸው ጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሐኑ ዘሪሁን እና ፀጋዬ ገብረ መድህን የሰላ ብዕራቸውን አስቀምጠው የልመና አኩፋዳቸውን እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል፡፡
ክቡር አርቲስት ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ደግሞ በሙዚቃ የረሀቡን ስፋት እና የሕዝቡን ተማጽኖ በተስረቅራቂ ድምጹ ለዓለም ሕዝብ ናኝቶታል፡፡ የኾነ ኾኖ በኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሀብ እየረገፉ መኾኑን አስመልክቶ ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1984 ሰፊ ዘገባ ሠራ፡፡
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ረሀቡን “በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀው ረሀብ” ካለው በኋላ “በምድር ላይ ለገሃነም ቅርቡ” ሲልም ነበር የኢትዮጵያውያንን ረሀብ የገለጸው። ዘገባውን ተከትሎም ለእርዳታ ማሠባሠቢያ ‘ላይቭ ኤይድ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው እና በርካታ ሙዚቀኞችን ያሠባሠበ የሙዚቃ ዝግጅት በዝነኛው አይርላንዳዊ ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍ መሪነት ተደገሰ፡፡ ዝግጅቱም በዚህ ሳምንት ሰኔ 28 ቀን 1977 በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲየም የእንግሊዝ ልዑል እና ንግሥት በተገኙበት ተከፈተ፡፡ ቦብ ዲላን፣ ሊድ ዘ ፔሊን እና ዘ ሁንም ደግሞ ከቦብ ጊልዶፍ ጋር የተሳተፉ ጉምቱ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡
በወቅቱ በሥፍራው ተገኝቶ ከተከታተለው ሕዝብ በተጨማሪ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሕዝብ በቴሌቪዥን ተከታትሎ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ እንዳደረገው ተዘግቧል፡፡ ከዝግጅቱም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለኢትዮጵያውያን ተሠባሥቧል፡፡
ዝግጅቱ ከእንግሊዝ በተጨማሪም በአሜሪካ ፊላደልፊያ ጆን ኦፍ ኬኔዲ ስታዲየምም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ 170ሺህ ሰዎች የታደሙበት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ‘ላይቭ ኤይድ’ን ተከትሎም በዓለም ላይ በርካታ የእርዳታ ማሠባሠቢያ የሙዚቃ ዝግጅቶች ተደረጉ፤ ታዲያ ለዚህ መሠረቱን የጣለው ይህ የሙዚቃ ትርዒት እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አጀንዳ እንዲኾን አስችሏል ሲል ያስነበበው ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ነው።
👉 ዘረኝነትን የሻረው ሕግና የጥቁሮች የእኩልነት መብት መከበር
በአሜሪካ ጥቁሮችን ከነጮች ዕኩል ያደረገው የሲቪል መብቶች ድንጋጌ የጸደቀው ሰኔ 25 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡ በአሜሪካ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረገ ተጽዕኖ ለበርካታ ዓመታት ተንሰራፍቶ ቆይቷል፡፡ ነጮች በሚማሩበት ትምህርት ቤት እና የሥራ መስክ ለጥቁሮች አይፈቀድም ነበር፡፡ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በአንድ አውቶብስ አይሄዱም፤ በመዝናኛ ሥፍራዎችም ተመሳሳይ ክፍያ ቢፈጽሙ እንኳ ተመሳሳይ ግልጋሎት አያገኙም፡፡ በጠቅላላው ነጮች ባሉበት ጥቁሮች መገኘት እንዳይችሉ ባልተጻፈ ሕግ ተደንግጎ ሲተገበር ቆይቷል።
36ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊንደን ጆንስን ይህን የዘረኝነት ሕግ ሽረው የሲቪል መብቶች ድንጋጌ በሕግ ያጸደቁት በዚህ ሳምንት ሰኔ 25 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ጆንሰን በዘመናዊቷ አሜሪካ ታሪካዊ የተባለለትን የዘር መድሎን የሚከለክለውን ድንጋጌ ሲፈርሙ በቀጥታ ከኋይት ሐውስ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ያገኘው ሰኔ 25 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡ ሕጉ ጥቁሮችን ከምርጫ ተሳትፎ የሚከለክለው አሠራር አስወግዶ መሪያቸውን መምረጥ እንዲችሉ የሚፈቅደው ድንጋጌ እና ሴቶችን ጨምሮ ሕዳጣን ( ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው) የማኀበረሰብ አባላትን ዕኩል መብት እንዲኖራቸው የሚፈቅደው ሕግም መጽደቁን ልብ ይሏል፡፡
ይህን የዕኩልነት መብት የሚያረጋግጠው ሕግ በ36ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በፊርማቸው ያጽድቁት እንጂ የምርጫ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ የተገደሉት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከእሳቸው ቀደም ብሎ እየጠነከረ የመጣውን የሲቪል መብቶች ሕግ መከበር ንቅናቄ ተከትሎ ከተመረጡ በሕግ ደንግገው እንደሚያስከብሩት የገቡት ቃል ነበር። እናም በዚያኑ ጊዜ ታዲያ ሊንደን ጆንሰን የጆን ኤፍ ኬኔዲ ምክትል እንደነበሩ ሒስትሪ ዶት ኮም በድረ ገጽ አስታውሷል፡፡
👉የኢንሱሊን ግኝት!
የስኳር በሽታ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ ህመም ነው። ህመሙ የሚከሰተው ሰውነት በደም ሥር ውስጥ ያለን ስኳር (ጉሉኮስ) በሙሉ በተገቢው መጠን ማመንጨት ሲሳነው ነው። በሽታው የልብ ድካምን፣ የደም መጓጎልን ፣ ዐይነ ስውርነትን፣ የኩላሊት ሥራ ማቆምን ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ በየዓመቱ 422 ሚሊዮን ያህል አዳዲስ ህሙማን ይመዘገባሉ። የስኳር በሽታ የሚከሰተው ኢንሱሊን ሳይመረት ሲቀር ወይም በአግባቡ ሳይሠራ ሲቀር እና ስኳር በደማችን ውስጥ ሲከማች ነው፡፡ በሽታውን ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በመከተል እና አካላዊ እንቅስቃሴ በመሥራት መቆጣጠር ይቻላል። የስኳር በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ጥራጥሬን መመገብ ጥሩ መፍትሔ እንደኾነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሆርሞን ኢንሱሊን ይባላል። ይህ ኢንሱሊን ደግሞ የሚመረተው ጣፊያ በተባለ የሰውነት ክፍል ውስጥ ነው። ኢንሱሊኑ በደም ውስጥ ያለው ስኳር ሰውነት የሚፈልገውን ኀይል እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።
ይህን ተፈጥሯዊ ኾርሞን በሰው ሠራሽ ኢንሱሊን ለመተካት ተመራማሪዎች ሌት ተቀን ታትረዋል፡፡ በመኾኑም የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጠበብቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ሠራሽ ኢንሱሊን ፈብረከው ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት ሰኔ 28 ቀን 1907 ዓ.ም ነበር፡፡ ኢንሱሊኑ ህመምተኞችን ለማከም የሚያስችል መድኃኒት ነው፡፡ ግኝቱም በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የስኳር ህመምተኞችን ሕይዎት የታደገ መድኃኒት መኾኑንም ከኖውሌጂ መጽሐፍ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!