
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 100 ተማሪዎቹን አስመርቋል።
በምረቃው ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እና ትምህርት ችግር ፈቺ፣ የፈጠራ ክህሎት እና ሃሳቦችን ያካተተ እንዲኾን ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
“የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚያሳካ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት መንግሥት ዘመኑን ለዋጀ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ልዩ ትኩረት መስጠቱንም” ተናግረዋል።
ከመጪው ዓመት ጀምሮ በአዲሱ ፖሊሲ መሠረት በደረጃ 8 (ፒ.ኤች.ዲ) የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና እና ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዛሬ ከተመረቁት መካከል የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቁመው ይኽም ኢትዮጵያ በቀጣናው ትብብሯን በማጠናከር የተሻለ ነገን በጋራ ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ተመራቂዎች በትምህርት እና ስልጠና ቆይታቸው ባገኙት እውቀት ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲያሸጋግሩም አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ.ር) በበኩላቸው ገበያ ተኮር መርህን በመከተል በሁሉም መስክ ብቁ የሰው ኃይል እያፈራን ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በዲጅታል የታገዘ የሥልጠና ሥርዓትን ለመከተል እና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመኾን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!