በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በቀጣይ ዓመት የተሻለ ገቢ መሰብሰብ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ።

33

ደሴ: ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ማኅበረሰቡ ስለ ግብር ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድግ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ግብር ከፋዮች፣ የከተማ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ሰራተኞች እና መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ኾነዋል።
በመድረኩ የከተማ አሥተዳደሩ የ2015/2016 የገቢ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የደረጃ ሐ እና ደረጃ ለ ግብር ከፋይ የኾኑት ይማም በላይ እና ሮዚና ሰይድ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ድርሻውን እየተወጡ እንደኾነ ተናግረዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ የግብር ትምህርት ቡድን መሪ ጦይባ ሁሴን ግብር ከፋዮች ግንዛቤ እና መረጃ እንዲያገኙ፣ ግብራቸውን በወቅቱ እና በታማኝነት እንዲከፍሉ የማስተማር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ መሐመድ ሰይድ በ2015/2016 የግብር ዘመን ከመደበኛ እና ከከተማ አሥተዳደር ገቢ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውሰው በቀጣይ በጀት ዓመትም የተሻለ ለመፈጸም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።

ማኅበረሰቡም የሚያጋጥሙ የታክስ ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ እና እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ገቢ ወሳኝ በመኾኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ:-አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ከተማን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“የኢንዱስትሪ ሽግግሩን የሚያሳካ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ለቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል” ሙፈሪሃት ካሚል