የጎንደር ከተማን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ።

28

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር “ሰላም ለሁሉም ፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የሕዝብ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አበበ ላቀው የሕዝብ የሰላም ኮንፈረንስ በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞችና ቀበሌዎች መካሄዱን ገልጸዋል።

ውይይቱ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

“አሁን በከተማችን የተገኘው አንፃራዊ ሰላም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተገኘ ነው” ያሉት ኃላፊው የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ዛሬም ነገም ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኅብረተሰቡን የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጥያቄዎችን፣ የሕዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃማነት ለማረጋገጥ፣ የማንነትና የራስ አሥተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ የሚቻለው ሰላማችን በአስተማማኝነት ደረጃ መገንባት ሲቻል ነው ብለዋል።

ስለዚህ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግሥት አሁን ያለውን የሰላም ችግር በስምምነት ሊፈታው ይገባል፣ የሰዎች እገታ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣ የኑሮ ውድነት መከላከልና ሌሎች የመልካም አሥተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በውይይቱ ወጣቶች ፣ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ማርቆስ ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ።
Next articleበኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በቀጣይ ዓመት የተሻለ ገቢ መሰብሰብ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ።