የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ልዩ መመሪያ አወጣ፡፡

31

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሦስት እግር የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በግራ በኩል ያለውን ሸራ እና በቀኝ በኩል የሚገኘውን መጋረጃ ሳያነሱ ማሽከርከር እንደማይችሉ የከተማው ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ እንደገለጹት በከተማው አገልግሎት የሚሰጡ የባለ ሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ለእይታ ግልጽ እንዲኾኑ የግራ ሽራና በቀኝ በኩል መጋረጃዎችን ከሰኔ 30/2016 ዓ.ም ጀምሮ ክፍት አድርገው እንዲያሽከረክሩ ታዟል።

ከአሁን በፊት በተደረገው የባጃጅ የስዓት ገደብ እገታ እና የተለያዩ ወንጀሎችን ማስቆም እንደተቻለ የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ በሕገወጥ መንገድ ያለ ታርጋ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፣ የከተማ ፍቃድ የሌላቸው እና በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ 56 ባጃጆች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ለቁጥጥር እንዲያመች፣ በወንጀል የሚጠየቁ እንዲታዩ እና ለተገልጋዩ ግልጽ እንዲኾኑ የግራ ሸራ እና የቀኝ መጋረጃ ክፍት አድርገው አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

ተግባራዊ በማያደርጉ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑንም ገልጸዋል።

ታርጋው በቅጣት የተፈታበት፣ የከተማ ፍቃድ የሌላቸው ባጃጆችን በከተማው ማሽከርከር እንደማይቻል እና ይህን ተላልፈው በሚገኙት ላይ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑን ኮሚሸነሩ አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያሳየው በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ5 ሺህ በላይ የከተማ ፍቃድ ያላቸው ባጃጆች ያሉ ሲኾን ከ500 በላይ የከተማ ፍቃድ የሌላቸው ባጃጆች ደግሞ ወደ ወረዳ መውጣታቸው ነው የተገለጸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከውጭ ሲገቡ የነበሩ 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን መረቁ።