“ከውጭ ሲገቡ የነበሩ 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

28

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በበጀት ዓመቱ የብድር አቅርቦቱን በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በፌዴራልም ኾነ በክልል ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ለዘርፉ ዕድገት የማይተካ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የዘርፉን ዕድገት ለማስቀጠል የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ በዘርፉ የሕግ እና አሠራር ማሻሻያዎች መደረጉን ገልጸዋል።

የሀገሪቱን የተዛባ የውጭ የንግድ ሚዛን ለማሻሻል የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ በመገባቱ ከውጭ ሲገቡ የነበሩ 96 ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካታቸውን ጠቁመዋል።

በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ባለፉት አሥር ወራት ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብቻ 42 ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡንም ነው የተናገሩት። ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱንም ነው ያስገነዘቡት።

የብድር አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ገልጸው ይህም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በአምራች ዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻን 10 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ አንስተዋል፡፡ በስትራቴጂክ ምርቶች ብቻ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏልም ነው ያሉት።

በውጭ ምንዛሬ፣ በኀይል እና በመሠረተ ልማት አቅርቦት ዙሪያ ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ምርት ፍላጎት ያላት ሀገር በመኾኗ በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራትን በተመለከተም በማኅበረሰቡ ዘንድ የተዛቡ ዕይታዎች እንዳሉ ገልጸው የኢትዮጵያ ምርት በሌሎች ሀገራት ገበያ ያለምንም ችግር እየተሸጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከፋብሪካ ምርት ሂደታቸው ጀምሮ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረገ ክፍተቶች ሲገኙ እርምጃ እንደሚወስድም ነው ያብራሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግጭቱ ይበቃል ወደ ሰላም ተመለሱ ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሁኗል” የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች
Next articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ልዩ መመሪያ አወጣ፡፡