“ግጭቱ ይበቃል ወደ ሰላም ተመለሱ ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሁኗል” የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች

29

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ሁሉም አካላት ተቀብለው እንዲተገብሩት በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ሰላምን ለማጽናት የካውንስሉ የሰላም ጥሪ ወቅታዊ እና አስፈላጊ መኾኑን ነው አርሶ አደሮች የገለጹት፡፡

በጦርነት ሀገር ይወድማል ያሉት አርሶ አደር ሁሴን ያሲን ብዙ ወንድሞቻችንን እና ልጆቻችንን አጥተናል ብለዋል፡፡ ሰላምን አጥብቀን ነው የምንፈልገው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከአሁን በኃላ ጦርነት በቃን የሚሉት የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሩ ሀገርን ማሳደግ የተሻለ እንደኾነም ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ ውድቀት ላይ ነን የሚሉት አርሶ አደሩ ሰላም ባለመኖሩ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቶ ችግር ውስጥ ከቶናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ “ግጭቱ ይበቃል ወደ ሰላም ተመለሱ ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሁኗል” ብለዋል አርሶ አደር ሀዋ ይማም ገበሬም አርሶ እንዲበላ፣ ነጋዴው እንዲነግድ፣ ተማሪው ትምህርቱን እንዲማር እና ልጆቻችን ወጥተው እንዲገቡ ሰላም የሚያስፈልግ በመኾኑ ሰላሙ እንዲረጋገጥ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡

በየትኛውም አቅጣጫ ቢኾን የሀገሪቱ ዜጎች በነጻነት እንዲኖሩ ማድረግ ይገባል፤ ለዚህም ምኞታችን ሰላም እንዲኾን ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሯ የሰላም ጥሪውን ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርገውም ጠይቀዋል፡፡

አርሶ አደር መኮንን ይመር የሰላም ጥሪው ወቅታዊ እና ተገቢ ነው፤ ያለሰላም የሚኾን ነገር ባለመኖሩ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደር መኮንን ውሎ ለመግባትም ኾነ የእለት ጉርስን ለማግኘት ያለ ሰላም የማይኾን በመኾኑ ለሰላም መስፈን መረባረብ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

አርሶ አደር ሀዋ ይማም የሰላም ጥሪውን እናቶች የፊት መሪ ኾነው እንዲሳካ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ነው ያብራሩት፡፡

ልጆቻችን ወጥተው ለመግባት ተቸግረው እናቶችም ተጨንቀው ነው የሚገኙት የሚሉት አርሶ አደሯ ከዚህ ጭንቀት ለመገላገል ለሰላም ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አርሶ አደር ግርማ ሰይድ በበኩላቸው የሰላም ጥሪውን ተቀብለን መንግሥት እና ሕዝብ ተናበው እና አንድ ኾነው አሁን ላይ ጠላት የኾነብንን ድህነት መታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአካባቢው ያሉ ወጣቶች ሰላምን መርጠው ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ይገባል ያሉት አርሶ አደሩ ለዚህም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከልቡ የመሥራት ኀላፊነት እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

አርሶ አደር ሁሴን ከበደ በበኩላቸው በተፈጠረው ችግር ሰብዓዊም ኾነ ቁሳዊ ውድመት መፍጠሩን ተናግረው አሁንም ሁሉንም ይቅር ብሎ ወደ ሰላም መምጣት እና የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን ጥሪ መቀበል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

እርስ በእርስ መከባበር ያስፈልጋል ያሉት አርሶ አደሩ አሁንም የቀረበውን ጥሪ አክብሮ ሰላም ለማምጣት ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ ነው የጠየቁት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ5 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎቹን አስመረቀ።
Next article“ከውጭ ሲገቡ የነበሩ 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል