በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ።

36

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ20 ሄክታር የደን ቦታ ላይ ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የችግኞቹ ተከላ የሚካሄደው በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት የደን መመናመንና መራቆት በሚታይባቸው በተለዩ የፓርኩ አካባቢዎች መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ ተናግረዋል።

በዚህም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት የቦታ ልየታና የመትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ማካሄድ መቻሉን ገልጸዋል።

ግራር ፣ ኮሶ፣ ወይራና ውጨና የተባሉ ሀገር በቀል የደን ችግኞችን በስካውቶች፣ በአካባቢው ማኅበረሰብና በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሠራተኞች የጋራ ተሳትፎ በመጪው ሐምሌ እንደሚተከሉ አስታውቀዋል፡፡

የሚተከሉት ችግኞችም የፓርኩን የእጸዋት ብዘሃ ሕይወት ለመጠበቅ እንደሚያግዙ አመልክተው፤ አስፈላጊው እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ግብረ ኀይል ከወዲሁ መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ክረምት በፓርኩ ክልል የተተከሉ ሀገር በቀል ችግኞች በአሁኑ ወቅት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን በተካሄደ ቆጠራ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

በፓርኩ ክልል በሚያዚያ ወር ተከስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰበት የጓሳ ሳርና የደን ሃብት አሁን ላይ እየጣለ ባለው የክረምት ዝናብ ማገገም መጀመሩን ጠቁመው ፤ የችግኝ ተከላው የፓርኩን ጥበቃ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበርካታ የብዝሃ ሕይወት ሀብቱ የሚታወቀው የሰሜን ብሄራዊ ፓርክ ከአንድ ሺህ 200 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙበት የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተዘገበው ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ የመሰሉ ብርቅዬ እንስሳት መኖሪያ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለክልሉ ሕዝብ ሰላም ሲባል የታጠቁ ወገኖች የሰላም ካውንስሉን ጥሪ እንዲቀበሉ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next article“የብዙ ምንጮች መፍለቂያ፣ የድንቅ ተፈጥሮ መገኛ፣ የእምቅ የቱሪዝም ባለቤት፣ የሀገር ሽማግሌዎች ምድር አርባ ምንጭ!” ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ