ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ሲባል የታጠቁ ወገኖች የሰላም ካውንስሉን ጥሪ እንዲቀበሉ ነዋሪዎች ጠየቁ።

57

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ሲባል የታጠቁ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና በንግግር እንዲፈቱ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በተከሰተው እና ለአንድ ዓመት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ክልሉ ለሰላም እጦት፤ ነዋሪዎችም ለሞት፣ ስደት እና እንግልት ተዳርገው ቆይተዋል። ቀድሞውንም ልዩነቶች በውይይት፣ በእርቅ እና በንግግር ማለቅ እንደነበረባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ወንድምን ከወንድሙ ያጋጨው፣ ለህልፈት ሕይዎት፣ ለንብረት ውድመት እና ለኑሮ ውድነት የዳረገው የእርስ በእርስ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ”ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ኮንፈረን ተካሂዷል።

በተደጋጋሚ ከተደረጉ ውይሰቶች እና ምክክሮች ማግስትም ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የሚያስችል የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ተቋቁሟል።

የሰላም ካውንስሉ ባወጣው መግለጫም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ለሕዝቡ ማኅበራዊ እረፍት እና መረጋጋት ሲሉ ተኩስ አቁመው ለውይይት እና ለንግግር እንዲቀመጡ ጥሪ አቅርቧል።

በሰላም ጥሪው ላይ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች የሰላም ጥሪው የሕዝቡን የልብ ትርታ ያዳመጠ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚኾን ነው ብለዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የታች ጋይንት ወረዳ ነዋሪ የኾነው ወጣት ሁናቸው በዜ ግጭቱ ለዜጎች መጎዳት ምክንያት የኾነ እና የኑሮ ውድነትንም ያባባሰ እንደኾነ ገልጿል። ወጣቱ ሰላም ፈላጊ መኾኑን የጠቆመው አስተያየት ሰጪ የሰላም ካውንስሉ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ውይይት ተደርጎ ወደ ቀደመ ሰላም መመለስ ጥሩ ነው ብሏል።

ችግሩ በውይይት ተፈትቶ በጫካ ያሉ ወንድሞችም ወደ ቤታቸው በሰላም ቢመለሱ ደስተኛ እንደኾነ ተናግሯል። ችግሮችን በውይይት፣ በእርቅ እና በንግግር መፍታት ክልሉን ወደ ሰላም እና ልማት ይመልሳል ነው ያለው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ እና የአዲስ ዘመን ከተማ ነዋሪው ወጣት ሰለሞን አንዳርጌ በበኩሉ የኅብረተሰቡን ሰላም እና ሠርቶ ማደርን ፈላጊነት ጠቅሶ ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወጣቶች መኖራቸውን ገልጿል።

የሰላም ችግሩ በውይይት ተፈትቶ በጫካ ያሉ ወንድሞች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ እና ሕዝቡም ሰላሙን እንዲያገኝ የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ፍላጎት እንደኾነ ነው የተናገረው።

በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ ነዋሪው አንዳርጌ በላይ በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች ቀድመው የጀመሩት ሥራ ባለመሳካቱ የተከሰተው ግጭት ሕዝቡን ለበርካታ ችግር ዳርጎት ቆይቷል ብሏል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በክልሉ ለተፈጠረው የሰላም እጦት ዘላቂ መፍትሄው እርቅ እና ውይይት በመኾኑ ተፋላሚ ወገኖች ለሕዝባቸው ሰላም ሲሉ የካውንስሉን ጥሪ ዋጋ ሰጥተው ወደ ሰላም እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleበስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገር በቀል ችግኞች ይተከላሉ።