“ከተማችን ለመኖር የምትመች እና አረንጓዴ የምትለብስ የምናረጋት እኛ ነን፤ ለዚህም ነው ችግኝ የምንተክለው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

42

አዲስ አበባ፡ ሰኔ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ በሚል መሪ መልዕክት የ2016 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቤተል መንዲዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የ2016 ዓ.ም የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የምንተክለው ዛሬን ብቻ አይደለም ነገን ጭምር እንጂ፤ መተባበር እና አብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት አይተናል ብለዋል የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

አዲስ አበባ ስትመሠረት አረንጓዴ ነበረች በከተማ መስፋፋት ያጣችውን ደን ለመመለስ እየሠራን ነው ብለዋል።

በከተማዋ የአረንጓዴ ተክል ትግበራ ተጠናክሮ የቀጠለ መኾኑን ያነሱት ከንቲባ አዳነች መትከል ብቻ ሳይኾን የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክበን ለፍሬ ልናበቃቸው ይገባል ነው ያሉት።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገኝተዋል።

ውብ እና አረንጓዴ የአዲስ አበባ ከተማን ገንብተው ለትውልድ እንደሚያስረክቡም ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።

“ከተማችን ለመኖር የምትመች እና አረንጓዴ የምትለብስ የምናረጋት እኛ ነን፤ ለዚህም ነው ችግኝ የምንተክለው” ብለዋል።

ለትውልድ የምናስተላልፈው አብሮ የመኖር እና የመሥራት እሴትን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ተክለናል ዘንድሮ ደግሞ በጋራ 20 ሚሊዮን ችግኝ እንተክላለን ነው ያሉት ከንቲባዋ።

ችግኝን በክረምቱ ሁሉም በየአካባቢው እና በሃይማኖት ተቋማቱ እንዲተክልም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አርባ ምንጭ በተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች፣ ድንቅ አዕዋፍ፣ አስደማሚ ተራሮች፣ የውኃ ምንጮች እምቅ ሀብት የታደለ እጅግ ተፈላጊ መዳረሻ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት አስተላለፉ።